AMN – የካቲት 16/2017 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊነትን ባከበረ መልኩ ሀገረ መንግሥትን ለመገንባት የጀመረው ሂደት ውጤታማ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ገለጹ።
በብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ የተቀመጡ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የሕዝብ ኮንፍረንስ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በህዝባዊ ኮንፍረንሱ በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ በብልጽግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ አቶ ይርጋ ሲሳይ፣ ብልጽግና ፓርቲ ሁሉንም አክብሮና አሳትፎ እውነተኛ መንገድ ይዞ እየተጓዘ ያለ ትልቅ ፓርቲ ነው ብለዋል።
ሁሉም አንድ ሆነው ተባብረው ሠርተው የሚኖሩባት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት እየሠራ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፓርቲው የሕዝብ ኃላፊነት ተሸክሞ ወደ ተግባር ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም ፈተናዎችን ወደ መልካም ዕድል እየቀየረ በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ መምጣቱን ገልጸዋል።
በሁሉም ዘርፎች ወደ አገልግሎት የገቡና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ብልጽግና መስፈንጠሪያ መሆናቸውን አንስተዋል።
በፖለቲካ ዘርፍ አሰባሳቢ ትርክቶች መምጣቸውን ጠቅሰው፣ ፓርቲው ቃሉን አክብሮ የሚፈጽም በመሆኑ በሁለተኛ መደበኛ ጉባዔው የተቀመጡ ውሳኔዎችንም በተግባር ያረጋግጣል ብለዋል።
ፓርቲው ሕዝቡን እንደ ትልቅ አቅም ተጠቅሞ አሳታፊ በሆነ መልኩ የሚሠራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አሰተዳዳሪና የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በበኩላቸው፣ በለውጡ መንግስት በዞኑ አዎንታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንደተቻለ ጠቅሰው፣ ዞኑ የተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መገኛ መሆኑን መግለፃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።