የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጦርነቱን ለማቆም ከሩሲያ ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ከመደረሱ አስቀድሞ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸውን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።
“ከሩሲያ ጋር ማንኛውም ውሳኔ ላይ ከመድረስዎ በፊት እባክዎ ሆስፒታሎችና አብያተ-ክርስትያናት መውደማቸውን እንዲሁም ንፁሀን ዜጎች፣ ህፃናት እና ወታደሮች መሞታቸውን በአፋጣኝ መጥተው ይመልከቱ” ሲሉ ነው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ለአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ይህ ጥሪ ከቀረበ በኋላ በትናንትናው እለት ሩሲያ ሰሚ በተባለ የዩክሬን ከተማ ላይ በሰነዘረችው የሚሳኤል ጥቃት 34 ንፁሀን ዜጎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ ከሟቾቹ መካከል 2ቱ ህፃናት ሲሆኑ 117 ሰዎች ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡
የሚሳኤል ጥቃቱን ፕሬዝዳንት ትራምፕ አስደንጋጭ ሲሉ የገለፁ ሲሆን ጀርመን ጉዳዩን ከጦር ወንጀል ቆጥራዋለች፡፡ ፈረንሳይም ጥቃቱን አጥብቀው ከኮነኑ ሀገራት መካከል እንደምትገኝ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡