ምንም እንኳን ስምምነቱ የእሳቸውን እና የቻይናውን ፕሬዝዳንት የመጨረሻ እውቅና የሚጠብቅ ቢሆንም በሁለቱ ሀገራት መካካል በለንደን የተካሄደው የንግድ ስምምነት በታሰበው ልክ መከናወኑን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ገልጸዋል፡፡
ትሩዝ በተሰኘው በራሳቸው የትስስር ገጽ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ላይ በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ ብርቅዬ ማዕድናትን ከቻይና ታገኛለች፣ በአንፃሩ የቻይና ተማሪዎችም የአሜሪካ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎችን ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡
በለንደኑ የስምምነት መድረክ ላይ ጎልቶ የወጣው ትልቁ ጉዳይ ለቴክኖሎጂ አጋዥ ነው የተባለላቸው ብርቅዬ የምድር ውስጥ ማዕድናትን ቻይና ወደ አሜሪካ መላክ አለባት የሚል ነበር፡፡
እንደ አልጀዚራ ዘገባ ቻይና የኤሌክትሪካ መኪናን ጨምሮ ስማርት ስልኮችን ለማምረት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጠውን ማዕድን አትልክም በሚል በአሜሪካ በኩል ስትወቀስ ቆይታለች፡፡
በአፀፋው አሜሪካ ሰሚኮንዳክተሮችን እና ከአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የተገናኙ የቴክኖሎጂ ሸቀጦች ወደ ቻይና እንዳይገቡ አድርጋለች፡፡
የቻይና ንግድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም የለንደኑ ስምምነት የፕሬዝዳንት ዢ ጂን ፒንግን የመጨረሻ ፈቃድ እንዳገኘ ተፈፃሚ አንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች አስደሳች የተባለለትን የስልክ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ በለንደን በተወካዮቻቸው አማካኝነት በአካል ያደረጉት የንግድ ስምምነት የሀያላኑ የንግድ ጦርነት መቋጫ ሊያገኘው ከጫፍ መድረሱን ያመላከተ ይመስላል፡፡