
AMN-ግንቦት 03/2017 ዓ.ም
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ሞስኮ የሰላሳ ቀናት የተኩስ አቁም ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ እንድታደርግ መጠየቃቸውን ተከትሎ ዩክሬንን ለቀጥተኛ ውይይት ጋብዘዋታል።
ፑቲን በቴሌቪዥን ቀርበው በተናገሩት ንግግር፤ ሩሲያ ወደ ዘላቂ ሰላም ለመድረስ ጠንካራ ውይይት የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል፡፡
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬይር ስታርመር ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን እና ከፖላንድ መሪዎች ጋር ሆነው ሩሲያ ከሰኞ ጀምሮ ለ 30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንድትተገብር ጫና ለማሳደር ወደ ኪየቭ ተጉዘዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮፍ ፤ሞስኮ ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ መመርመር እንደሚያስፈልጋት በመግለጽ ጫና ለመፍጠር መሞከር ከንቱ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል ።
ቭላድሚር ፑቲን ከዩክሬን ጋር በቱርክ ኢስታንቡል ውይይት እንደሚጀመር እና በጉዳዩ ላይ ከቱርክ ፕሬዝደንት ሬሲብ ጣይብ ኤርዶኻን ጋር እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል፡፡
ኪየቭ ለቀረበላት ግብዣ ምላሽ አለመስጠቷን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡