AMN – የካቲት 17/2017 ዓ.ም
129ኛው የአድዋ ድል በዓል አከባበር የሀገራችንን አንድነትና ህብረት በሚያሳይና ኢትዮጵያን በሚያጎላ መልኩ መከበር እንደሚገባ የመከላከያ ሠራዊት ስነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ገለጹ፡፡
በመጪው የካቲት 23 ቀን ለ129ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓል አከባበር በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የመከላከያ ሠራዊት ስነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን የዘንድሮው የአድዋ በዓል “አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ሀሳብ ከባለድርሻ አካላትና ከመላው ህዝብ ጋር በጋራ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ገለጸዋል፡፡
አድዋ፣ የአንድነታችንና የህብረታችን ማሳያ፣ ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪን ያሸነፉበት ብቻ ሳይሆን ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት መሆኑን የገለፁት ጀኔራል መኮንኑ፣ በዓሉን ስናከብር ጀግኖቻችን እየዘከርን ህብረታችንን በሚያጎሉ ነገሮች ላይ በማተኮር ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በዓሉ በዳግማዊ ምኒልክ ሀውልትና በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም የሚከበር ሲሆን፣ በተጨማሪም በመላው ሀገራችን፣ የሀገራችን ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች በሚገኙባቸው ቦታዎች ሁሉ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁንም መናገራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የትሰስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡