AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም
ፌስቲቫሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት በድምቀት ተከፍቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያ የብዝሀ ባህል ባለጸጋ ነች፣ እነዚህን ባህሎች ለበጎ ነገሮች ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
ይህ ሲሆን ለሀገር ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖራቸው እና ብሄራዊነትን ለማስረጽ እንዲሁም ለወል ትርክት መሰል መርሃ ግብሮች የላቀ አስተዋጽኦ ስለሚኖራቸው፣ በፌስቲቫሉ ላይ በመሳተፍ ለትውውቅ እና አብሮነት ልንጠቀምበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ በበኩላቸው ባህል ኢትዮጵያውያን በጋራ እና በመከባበር እንዲኖሩ የላቀ አበርክቶ እያደረገ ያለ መሆኑን ገልጸው፣ መሠል መድረኮች ካላቸው ፋይዳ አንጻር በትኩረት እንዲከበሩ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመላ ሀገሪቱ በተከናወነው የባህል ሳምንት ፌስቲቫሎች ላይ ከ6 ሚሊየን በላይ ህዝብ ቀጥተኛ ተሳታፊ መሆኑንም ገልጸዋል።
መሰል መድረኮችን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን እና በዘርፉ ለሚከናወኑ ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሂሩት ካሳው ዘርፉን በሚገባ ለመምራት የተለያዩ ፓሊሲዎችን በመቅረጽ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በዚሁ መሠረት በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

ዘርፉን ለማበረታት እና ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም ገልጸዋል።
በፌስቲቫሉ መላው ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ለማድረግ ጥረቶች መደረጋቸውን እና መድረኩ የእርስ በርስ ትውውቅ ለመፍጠር እንዲረዳ ተደርጎ መዘጋጀቱን አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ አማካኝነት የተዘጋጀው የባህል ሳምንት ከየካቲት 21 እስከ 23 በጊዮን ሆቴል ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተመላክቷል።
”ባህሎቻችን የወል ትርክት አምባ” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ በጀመረው የባህል ሳምንት፣ የኢትዮጵያን ህዝቦች ባህላዊ አልባሳት፣ ምግቦች፣ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ዘፈኖች፣ ጭፈራዎች፣የሀይማኖቶች መገለጫዎች፣ የተለያዩ ዕደ ጥበባት እና ሌሎች ባህላዊ ሀብቶች ለዕይታ ቀርበዋል።
በሀብታሙ ሙለታ