18ኛው የቶኪዮ ማራቶን በቀጣዩ እሁድ በጃፓን መዲና ቶኪዮ ይካሄዳል

You are currently viewing 18ኛው የቶኪዮ ማራቶን በቀጣዩ እሁድ በጃፓን መዲና ቶኪዮ ይካሄዳል

AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም

18ኛው የቶኪዮ ማራቶን በቀጣዩ እሁድ በጃፓን መዲና ቶኪዮ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

በዚህ ውድድር አገራችንን ወክላ የምትወዳደረው አትሌት ሱቱሜ አሰፋ የራሷን እና የቦታውን ሪከርድ ለማሻሻል መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡

ውድድሩን ለማሸነፍ ግምት ካገኙ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው ሱቱሜ አሰፋ፣ ከምትገኝበት ቶኪዮ ከተማ ከኤ ኤም ኤን ጋር በስልክ ቆይታ አድርጋለች፡፡

ከአሰልጣኟ ብርሃኑ መኮንን ጋር ከቀናት በፊት ቶኪዮ የደረሰችው ሱቱሜ የቦታውን እና የራሷን ፈጣን ሰዓት ለማሻሻል መዘጋጀቷን የገለጸችው ሱቱሜ፣ ውድድሩን ለማሸነፍ በሚያስችል አቋም ላይ እንደምትገኝ ም ገልጻለች፡፡

የባለፈው ዓመት ውድድሩን ስታሸንፍ የቦታውን እና የራሷን ሪከርድ ያሻሻለችው ሱቱሜ በአወዛጋቢ ውሳኔ በፓሪስ ኦሊምፒክ ሳትሳተፍ መቅረቷ ይታወሳል፡፡ የእሁዱ ውድድር በመጪው ዓመት መጀመሪያ በቶኪዮ በሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ሚኒማ ከሚሟላባቸው ሜጀር ማራቶኖች አንዱ ነው፡፡

የመጀመሪያ የሜጀር ማራቶን ውድድሯን በ2020 ቶኪዮ ላይ አድርጋ ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ሱቱሜ፣ ለሶስተኛ ጊዜ ቶኪዮ ላይ እሁድ ሊነጋጋ ሲል ትሮጣለች፡፡ የቶኪዮ ውድድሩን በፈጣን ሰዓት አሸንፋ በኦሊምፒክ ያጣችውን ተሳትፎ በዓለም ሻምፒዮና ማሳካት እቅዷ መሆኑን ሱቱሜ ለኤ ኤም ኤን ገልጻለች፡፡

ውድድሩ የሚጠናቀቅበት ቦታ ሙቀት እስከ 20 ድግሪ ሴንትግሬድ እንደሚደርስ የተናገረው ደግሞ አሰልጣኟ ብርሃኑ መኮንን ነው፡፡ ሙቀቱ ከፍ ያለ ቢሆንም የሱቱሜ ዝግጅት ለማሸነፍ የሚያበቃት ነው ብለዋል፡፡

ከዋና ዋና የማራቶን ውድድሮች አንዱ በሆነው የቶኪዮ ማራቶን፣ ከሱቱሜ አሰፋ ባሻገር ትዕግስት ከተማና ጎቲቶም ገብረስላሴ ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም፡፡ ልክ የዛሬ ዓመት የተካሄደውን የዱባይ ማራቶን በ2 ሰዓት ከ16 ደቂቃ ከ07 ሰከንድ በበላይነት ያጠናቀቀችውና የበርሊን ማራቶን አሸናፊዋ ትዕግስት ከተማ ተጠባቂዋ አትሌት ናት፡፡

የ2022ቱ የአሜሪካ ዩጂን ዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዋ ጎቲቶም ገብረስላሴ እንዲሁም የፍራንክፈርት ማራቶን አሸናፊዋ ሐዊ ፈይሳ ሌሎች የሚጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡

የ2021ዱ የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊዋ ብርጊድ ኮስጌ ከውድድሩ ውጭ መሆኗ ተረጋግጧል፡፡ የ2023 አሸናፊዋ ሮዝሜሪ ዋንጅሩ ለሱቱሜ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደምትሆን ተገምቷል፡፡

የወንዶቹን ውድድር ኬንያዊው ቤንሰን ኪፕሩቶ ለማሸነፍ ቀዳሚውን ግምት ቢወስድም ኢትዮጵያውያኑም ቀላል ግምት አልተሰጣቸውም፡፡ የ2019ኙ እና የ2020ው ቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ብርሃኑ ለገሰ ለሶስተኛ የቶኪዮ ድል ጃፓን መዲና ቶኪዮ ደርሷል፡፡

የባለፈው ዓመቱን የሲቪያ ማራቶን ሲያሸንፍ የዓለማችን ሰባተኛውን ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበውና በፓሪስ ኦሊምፒክ አራተኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰው ደረሳ ገለታ ሌላው የሚጠበቅ አትሌት ነው፡፡

የሀንጋሪ ቡዳፔስቱ የዓለም ሻምፒዮና የነሀስ ሜዳሊያ አሸናፊው ልዑል ገብረስላሴን ጨምሮ ታደሰ ታከለና ዳዊት ወልዴን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች የቶኪዮ አሸናፊ ለመሆን ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ፡፡

በታምራት አበራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review