AMN-ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለብዝኃነት ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩና መጻኢ ዕድሎችን በሚወስኑ የጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመቆም እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታውቋል፡፡
19ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ም/ቤትና የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
በኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊ ወ/ሮ ባንቺይረጋ መለሰ፣ በፌዴራሊዝምና ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ተቀራራቢ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲኖር ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የሥልጠና መድረኩ ዋና ዓላማም ንቃተ ሕገ መንግሥትና የፌዴራል ሥርዓት በወጣቶች እና ሴቶች ዘንድ በማጎልበት እና ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ለሰላም ግንባታ ያለውን አስተዋጽዖ በየደረጃው ለሚገኙ የተለያዩ የኀብረተሰብ ክፍሎች የአስተምህሮ ሥራ በመሥራት የተቀራረበ ግንዛቤ እና ዕውቀት እንዲያዝበት ማድረግ ነው ብለዋል።
በዓሉን ሲከበር በሕዝቦች መካከል አገራዊ አንድነት ሥር እንዲሰድና እንዲዳብር የሚያደርጉ ተግባራትን መሥራት እንደሚገባ ጠቁመው የብዝኃነት ባህልን በማዳበር እና በብዙኃነቶች መሀከል እኩልነትን በማረጋገጥ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የበለጠ እንዲቀራረቡ፣ ወንድማማችነትና እህታማማችነት እንዲጎለብት ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በመድረኩ ላይ ኀብረ ብሔራዊ ፌዴራል በኢትዮጵያ ተግዳሮቶቹና የመፍትሔ ሀሳቦቹ በሚል ርዕስ የሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ማእከል ዋና ዳይሬክተር በዶ/ር ኃይለየሱስ ታየ እና በኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በአቶ በላይ ወዲሻ ፅሑፍ ቀርቦ ውይይት መካሄዱን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።