AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም
ፌስቲቫሉ ከነገ የካቲት 22 እስከ 30 2017 ዓም እንደሚኬሄድ ፌደራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በስፖርት ፌስቲቫሉ የ12ቱም ክልሎች፣ ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል ፖሊስ ስፖርተኞች በ10 የስፖርት ዓይነቶች እንደሚሳተፉ ተመላክቷል፡፡
በአቃላይ በውድድሩ 1 ሺህ 692 ስፖርተኞች በተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 154 ወንዶች እና 538 ሴቶች እንደሚሳተፉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል ተናግረዋል፡፡
የስፖርት ፌስቲቫሉ 116ኛ የኢትዮጵያ ፖሊስ ምስረታን ምክንያት በማድረግ እንደሚካሄድ ያመለከቱት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ፣ የኢትዮጵያ ፖሊስ ቀንን ምክንያት በማድረግም ሚያዚያ 26 የማጠቃለያ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

በስፖርታዊ ውድድሩ አሸናፊ ስፖርተኞች ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ ውድድር ላይ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች እንደሚሳተፉም አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ስፖርት ቡድን በፌስቲቫሉ በ8 የስፖርት አይነቶች እንደሚወዳደር እና ለውድድሩ ጥሩ ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስፖርት ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ያረጋል ሙሉ አስታውቀዋል፡፡
ነዋሪው ፣የስፖርቱ ማህበረሰብ እና የተለያዩ አካላት በተለያዩ ሜዳዎች የሚደረጉትን ውድድሮች በመመልከት እና በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ፌደራል ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሰለሞን በቀለ