19ኛው የናይል ቀን ከነገ በስትያ በአዲስ አበባ ይከበራል

You are currently viewing 19ኛው የናይል ቀን ከነገ በስትያ በአዲስ አበባ ይከበራል

AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም

19ኛው የናይል ቀን “የናይል ትብብርን ማጎልበት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም የፊታችን ቅዳሜ ይከበራል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) እና የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎረንስ አዶንጎ(ዶ/ር) በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስትሩ እንዳሉት በዕለቱ የናይል ትብብር ኢኒሼቲቭ አባል ሀገራት ክንዋኔዎችና ቀጣይ ሥራዎች ላይ ምክክር ይደረጋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ተፋሰስ በጋራ የመበልጸግና ህዝብን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ የትብብር መርህን ተከትላ እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

መድረኩ ሀገራት በድንበር ዘለል ውሃ ሀብቶች የጋራ ልማትና አጠቃቀም ማዕቀፍ ትግበራ ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት እና የባህል ልውውጥ የሚያጠናክሩበት ሁነት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የናይል ትብብር ኮሚሽንን ለማቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች የመሪነት ሚናዋን ጠቅሰው፤ ለተፋሰሱ ሀገራት ልማትና ብልፅግና እየሰራች ስለመሆኑ የታዳሽ ኃይል አቅርቦቷን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ ዋና ዳይሬክተር ፍሎሬንስ አዶንጎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ቀኑ የተፋሰሱ ሀገራት ለጋራ ልማትና ብልፅግና በጋራ የሚመክሩበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋራ የውሃ ሃብትን በፍትሃዊነት በመጠቀም የህዝባቸውን የልማት ፍላጎት የሚመልሱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማቶችን በጋራ ለመስራት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 1999 የተመሰረተው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የውሃ ሀብትን በትብብር ማዕቀፍ ማልማት፣ ዘላቂ ቀጣናዊ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢኒሼቲቩ አባል ሀገራት በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመምከር፣ አዳዲስ ሀሳቦችን ለመለዋወጥ እና አንድነታቸውን ለማጠናከር የናይል ቀንን እ.አ.አ ከ2007 ጀምሮ በማክበር ላይ ናቸው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review