AMN – ታኅሣሥ 11/2017 ዓ.ም
በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በአርባምንጭ ከተማ በድምቀት የተከበረው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የታለመለትን ዓላማ ከፍ ባለደረጃ አሳክቶ መጠናቀቁን የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገልጸዋል፡፡
በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ኅብረብሔራዊ አንድነት እና የሕዝቦችን ትስስር በሚያጠናክር መልኩ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደተከበረም አስታውሰዋል፡፡
“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረው ይህ በዓል ወንድማማችነትን፣ አብሮነትንና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሠሩ እና የዘንድሮው በዓል ካለፉት በዓላት በተለየ ሁኔታ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ደረጃ በሚመጥን መልኩ ከፍ አድርጎ ማክበር እንደተቻለ ጠቅሰዋል።
በዓሉ የhገራችንን በጎ ገጽታ መገንባት የተቻለበት ሆኖ አልፏል ያሉት አፈ ጉባኤው፣ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቱባ ባህላቸውን፣ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን፣ መተሳሰባቸውን እና ታሪካቸውን በአደባባይ ለመላው ዓለም ማሳየት የቻሉበት እንዲሁም ብዝኀነታችን ውበታችንና አንድነታችን መሆኑን በግልጽ ያሳየንበት በዓል ነውም ብለዋል።
አቶ አገኘሁ አያይዘውም የበዓሉን ዓላማ መሠረት በማድረግ የአዘጋጁን ክልል ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፀጋዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች፣ ምቹ የኢንቨስትመንት ቦታዎች፣ መኅበራዊ እና ባህላዊ ሃብቶች በስፋት ማስተዋወቅ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በዓሉ የክልሉን የኢንቨስትመንት እና የልማት ሥራዎች ለማነቃቃት ትልቅ እድል እንደፈጠረም አመላክተዋል፡፡
አፈጉባኤው በዓሉ ከፍ ባለደረጃ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለደቡብ ክልል መንግሥት እና ሕዝብ፣ ለሁሉም የፀጥታና ደኅንነት አካላት፣ ለሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የሕገ መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወ/ሮ ባንቺይርጋ መለሠ አጠቃላይ የበዓሉን አከባበር አስመልከቶ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽ/ቤት ማኔጅመንትና አስተባበሪ ኮሚቴ አባላት ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።
19ኛው የኢትዮጵያ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በሁሉም ክልሎች፣ በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች፣ ከሀገር ውጭ ከአስር በላይ በሚሆኑ ኢምባሲዎች እና ቆንስላዎች በድምቀት እንደተከበረ በሪፖርቱ መዳሰሱን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።