AMN – የካቲት 21/2017 ዓ.ም
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትንና የብሔራዊነት ትርክትን ለማጠናከር የጎላ አበርክቶ እንደነበረው የአፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።
በዓሉ የኢትዮጵያን ቀጠይ ርእይ ለመሰነቅ ያግዛል ያሉት አቶ አገኘሁ ይህ በዓል የብዝኀ ማንነታችን ማረጋገጫ፣ የብሔራዊነት ትርክት መሠረት መጣያና ለተጀመረው አገር አቀፍ ምክክር ጉልበት ሆኖ ለማገልገል የራሱን አሻራ እንደሚያሳርፍ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል::
አፈጉባኤው 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእውቅና እና የማጠቃለያ መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት በዓሉ የአስተናጋጁን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገጽታ ለመገንባት፣ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ከተያዘላቸው ጊዜ ቀደም ብለው ለማጠናቀቅና የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጎልበት እንዳስቻለ አመላክተዋል።
የበዓሉ መከበር አንዱ ዓላማ ዜጎች በሕገመንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሆነ ጠቁመው በዓሉን ምክንያት በማድረግ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት፣ ከፌዴራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደሮች ሰፊ ቁጥር ያለውን ሕዝብ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን መናገራቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት መረጃ ያሳያል::
19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “አገራዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደተከበረ ይታወሳል::