ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ በጀት ዓመቱ ክንውን

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ በጀት ዓመቱ ክንውን

ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 42ኛ መደበኛ ስብሰባውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት አካሂዷል፡፡ የምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል መንግስት የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን መነሻ በማድረግ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች የተለያዩ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ሰንዝረዋል፡፡

የህዝብ እንደራሴዎች በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ የስንዴ ፍጆታን በሀገር ውስጥ በመሸፈን፣ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በመስራት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በማጠናቀቅ፣ በኮሪደር ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ እና በሌሎች መስኮች የተገኙ ውጤቶችን አድንቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ስልጣን በሀይል ለመያዝ የሚፈልጉና የኢትዮጵያን ጥቅም ከሚጎዱ ሀይሎች ጋር ግንባር ፈጥረው የሚሰሩትን በማጋለጥ፣ ከታጠቁ ሀይሎች ጋር ያለውን ችግር በድርድር ለመፍታት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በፌዴራል መንግስትና ህወሓት (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) መካከል የተደረሰውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በማፅናት እንዲሁም ሀገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆንና በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱ እንዲጀመር ምን እየተሰራ ይገኛል? የሚሉ ከሰላም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በመቅረፍ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ምን እየተሰራ ነው የሚሉና ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ እኛም ለቀረቡት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡትን ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው የሰላምና ፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ ስሁት ከሆነ የፖለቲካ እሳቤ ይመነጫል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ሀገሪቱ ውስጥ የስንፍና ፖለቲካ ተበራክቷል፡፡ ይህም ግጭት፣ ፀብና ተቃርኖ እየወለደ ነው፡፡ የፖለቲካ ሊሂቃንን ብናይ ስራ ሳይሰሩና ሳያገለግሉ ግጭት በመፍጠር ትርፍ ለማግኘት እየጣሩ ነው፡፡ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በሀይል ለማስወገድ የሚፈልጉ ሀይሎች እንዳሉና ፍላጎትን በግድያ ለማሳካት የሚደረግ ጥረት መቆም እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ ኃላቀርነት፣ ዘረኝነት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነትና የሀገር ብሔራዊ ጥቅምን አለማስቀደም ሰላም እንዳይፈጠር እንቅፋት መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በአውስትራሊያ አንድ አደገኛ ጭልፊት ተገኝቷል፡፡ እሳት ጫሪ የሆነው ጭልፊት አንድ ቦታ እሳት ሲቀጣጠል ወደ ሌላ ቦታ በመውሰድ በማቀጣጠል እሳቱን ያባብሳል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት እሳቱን ሸሽቶ የሚሄድ በራሪ የሆነ አካል ሲያገኙ ለመብላት ነው፡፡  ልክ እንደዚያ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት ሲፈጠር ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶችን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ሰላምን ለማስፈን ማህበረሰቡ “አትግደሉኝ”፤ በእሱ ስምም ሰው እንዳይገደል “አትግደሉልኝ፤ እናንተም አትሙቱልኝ፤ ሰላም እፈልጋለሁ” ማለት ይጠበቅበታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንንም በቅርቡ የአማራ ህዝብ አደባባይ በመውጣት አሳይቷል፡፡ ሌላውም ህዝብ በተመሳሳይ መንገድ ሰላም የማይፈልጉ ሀይሎችን በቃኝ ማለት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም፤ ነገ ምርጫ ሲመጣ ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን እንደሰሩና ህዝብን በምን መልኩ እንዳገለገሉ መጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ከታች አገልጋይነትን ያልጀመረ፤ ስልጣን ይዞ በትልቅ ደረጃ ሊያገለግል አይችልም ብለዋል፡፡

“ሰላም ሁሌም አንፃራዊ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር አይደለም፤ ሁሌ ስራ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በለውጡ የመጀመሪያ ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች ቆመዋል፤ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ብዙ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች ቀንሰዋል፡፡ ነገር ግን አንድ ጊዜ ሰላም የለም ብሎ “ጭንቅላቱ ላይ ያስገባ ሰው” ቀደም ሲል ከነበረው እያነፃፀረ አሁን ሰላም አለ ሊል አይችልም፡፡ አንፃራዊ ሰላም ባይኖርማ በግብርና፣ ማዕድንና ሌሎች ዘርፎች ዕድገት አይመዘገብም ነበር፡፡ መንግስትም ያለው ሰላም የተሟላ እንዲሆን ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በለውጡ ሂደት ከባድ ፈተናዎች እንዳጋጠሙ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ለውጡ ኢትዮጵያን ከመፍረስ ታድጓል፡፡ ይህም የተገኘው የሪፎርሙ መንግስት በተከተለው ብልሃት የተሞላበት አካሄድ ነው ብለዋል፡፡

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ትግበራን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ ስምምነቱ ለትግራይ ህዝብ እፎይታ ፈጥሯል፡፡ እናቶች ልጆቻቸውን በየቀኑ በጦርነት ከማጣት ታድጓል፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ መንግስት እያሸነፈ እያለ፣ “ሰላም ይበልጣል” ብሎ ውጊያ ያቆመበት ለሀገርም፤ ለሌሎች ሀገራትም ልምድ መሆን የሚችል የፖለቲካ ባህል ያሳየበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ቆመው የነበሩ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡ መንግስትም ተመስርቷል ሲሉ በስምምነቱ የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል፡፡

የጦርነት ተፈናቃዮችን በተመለከተ ከራያና ፀለምት ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ከወልቃይት የተፈናቀሉትን ማስመለስና ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት፣ የተሀድሶ ስልጠና መስጠትና ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራዎች ይቀራሉ፡፡ መንግስት ተፈናቃዮች መመለስ እንዳለባቸው የፀና አቋም እንዳለውና ለዚህም በሁሉም ወገን ያሉ አካላት ተባባሪ መሆን አለባቸው፡፡ ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታት ተግባርም መፈፀም አለበት፤ ይህ አለመሆኑ ልማትና ክልሉን ይጎዳል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች አንዳንድ ጊዜ የፌዴራል መንግስት ችግር አድርጎ ማየት ስህተት ነው፡፡ የፌዴራል መንግስት ትግራይ ላይ ያለውን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል፡፡

በተያያዘም የትግራይ ህዝብ መቶ በመቶ ጦርነት አይፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ የዓለም አቀፍ ሁኔታ እና የዘመኑን የውጊያ ስልት ካለመገንዘብ አንዳንድ ጦርነት ለማንሳት የሚፈልጉ ሀይሎች አሉ፡፡ ውጊያውን “የሚያግዙን ሰዎች እና ሀገራት አሉ” የሚለው ግምገማ ስህተት ነው፡፡ የትግራይ ክልል የሚያስፈልገው ሰላም በመሆኑ የኃይማኖት አባቶች ግጭት እንዳይፈጠር እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክሩን ሂደት በተመለከተም፣ ምክክሩ ሁሌም የማይገኝና በኢትዮጵያ እንዲደረግ ሲለመን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን የመጣውን ዕድል መጠቀም ይኖርብናል። የትግራይ ህዝብም መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች እንዲፈቱለት ወደ ውይይት መግባት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ዲፕሎማሲ

ዓለም ኢ-ተገማች በሆነ መንገድ፣ ጠዋት ውጊያ፤ ከሰዓት እርቅ ወይም ከሰዓት ውጊያ፤ ጠዋት እርቅ ለመገመት በሚያስቸግር መንገድ እየሄደ በመሆኑ በጥንቃቄ ማየት ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ለዚህም ኢትዮጵያ ከወዳጅ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፣ ወዳጅ ካልሆኑት ጋር ያለውን በማለዘብ፣ ሚዛናዊና ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስጠብቀውን መንገድ በመምረጥ እንጓዛለን ነው ያሉት።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት በተመለከተም ኢትዮጵያና ጎረቤቶቿ ህልውናቸው የተሳሰረ ነው፡፡ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላት ድንበር በግልፅ ያልተቋጨ በመሆኑ ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት እየሰራ በመሆኑ ጊዜውን ጠብቆ እየሰመረ መሄዱ አይቀርም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ የኢትዮጵያ ሰላም ማጣትም ሆነ መጎዳት ጎረቤት ሀገራትንም አብሮ የሚጎዳ ነው፡፡ እንዳትጎዳና እነሱም ሉዓላዊነታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ የኢትዮጵያን ፍላጎት ማየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፡፡ የባህር በር ካላገኘች ግን ሀገር መሆን አትችልም፤ ይህ በእነሱ ወገን መከበር አለበት፡፡ አብሮ ለመኖር ሰጥቶ መቀበል ያስፈልጋል፡፡” ሲሉ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ጥያቄው ምላሽ የሚያገኝበት ዕድል እንዳለ አንስተዋል፡፡

በኤርትራ በኩል [ከኢትዮጵያ ጋር] ውጊያ እንደሚነሳ የሚነገሩ ወሬዎች እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን በኢትዮጵያ በኩል አንዲት ጥይት አይተኮስም፡፡ የኤርትራም ሆነ ሌሎችም የጎረቤት ሀገራት ህዝቦች የኢትዮጵያ ህዝብ ወንድም ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሰላም ተባብሮ ማድግ ነው የምትፈልገው፡፡ በሰላም እንድትኖር የማይፈልጉ ካሉ ግን ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት ብለዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አልቋል፤ ሆኖም ከመመረቁ በፊት ረብሻ ለመፍጠር የሚሞክሩ እንዳሉ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን እንዳይመረቅ የሚያስችል ነገር የለም፤ ክረምቱ ሲያልቅ ይመረቃል ብለዋል። የህዳሴ ግድብ ለሱዳንና ግብፅ በረከት እንጂ በፍፁም ጉዳት አያመጣባቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሀይል ልማት ለሁሉም ጎረቤቶች የሚዳረስ ነው፡፡ የግብፅ አስዋን ግድብ አንድ ሊትር ውሃ አልቀነሰም፡፡ ወደፊትም ኢትዮጵያ የግብፅ እህትና ወንድም ህዝብ ጉዳትን ማየት አትፈልግም፤ ተባብሮ ለማደግ ዝግጁ ናት። የግብፅ፣ ሱዳንና የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መንግስታት ግድቡ ሲመረቅ የደስታው ተካፋይ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት

በኢትዮጵያ አንዱና ትልቁ ክፍተት የመኖሪያ ቤት ችግር ነው። ቤት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ “ቤት ያላቸው የሚመስሉ” የቤት መስፈርትን በማያሟላና መፀዳጃ በሌለው ቤት ውስጥ የሚኖሩትንም እንደሚጨምር ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣  ይህንንም ለመፍታት በመንግስት፣ በግል እና በመንግስትና በግል ትብብር በርካታ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታትም 1 ሚሊዮን ቤቶች ተሰርተዋል። አሁን ላይ ከ265 ሺህ በላይ ቤቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ወደፊት መንግስት በቤት ግንባታው ዘርፍ በሰፊው እንደሚገባበት ጠቁመዋል፡፡

ጤና

በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም የሚታዩ ጉድለቶች መፈተሽ አለባቸው፡፡ በጤና ባለሙያዎች የሚነሱ ጥያቄዎችንም አቅም በፈቀደ መጠን መመለስ ያለባቸው እንደሆነ መንግስት እንደሚያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

ትምህርት

በተያዘው ዓመት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በቅድመ መደበኛና 29 ሺህ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ህጻናት ትምህርት ቤት እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ህጻናት የሚውሉበት የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል፤ መምህራን ተቀጥረዋል፡፡ ይህም በትምህርት ዘርፉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገለፁት፡፡ 

ሙስና

ከሙስና ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መንግስታዊ ሙስና የለም፡፡ ነገር ግን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ቀላል ሙስና (Petty corruption) ይታያል፡፡ ለዚህም ዋናው መፍትሔ የመንግስት አገልግሎትን ሪፎርም ማድረግ መሆኑን በማመን ስራዎች ተጀምረዋል፡፡ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 23 ተቋማት ወደ አንድ እንዲመጡ በማድረግ 124 አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው፡፡ በዚህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከ90 በመቶ በላይ ተገልጋዮች እርካታ አላቸው፡፡ በአንድ ቦታ ያለውን አገልግሎት በማስፋት እስከ መስከረም ወር መጨረሻ 2018 ዓ.ም በ18 ቦታዎች አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ኢኮኖሚን በተመለከተ

ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምላሽ እና ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢኮኖሚ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የግብርና ልማት ሥራ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ የአገልግሎት ዘርፍ፣ የፋይናንስ ዘርፍ፣ የገቢ እና የዕዳ ሁኔታ፣ የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት፣ የማዕድን ማዳበሪያ እና የጋዝ ምርትን እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ባደረገው ምላሽ እና ማብራሪያቸው አስቀድመው ያነሱት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን የተመለከተ ነው፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ የነበሩ አራት ዋና ዋና ስብራቶች ወደ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመግባት አስገዳጅ ሁኔታዎች እንደነበሩ አንስተዋል፡፡ ይህንንም ሲያብራሩ፤ “የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶች፤ የመጀመሪያው በሥራ አጥነት፣ በዋጋ ግሽበት፣ በወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን መጓደል ሊገለፅ የሚችል ነው፡፡ ሁለተኛው የስራ አካባቢው ለግሉ ዘርፍ ምቹ አልነበረም። ሦስተኛው ምርታማነት ነው። በግብርናም በኢንዱስትሪም ምርታማነታችን ውስን ነበር። ይህም ለበርካታ ተግዳሮት ዳርጓል። አራተኛው ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሁኔታን አልፈጠርንም፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ጨክነን በመፍታት የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቱን መፍታት እንችላለን ብለን ነው ወደ ተግባር የገባነው” በማለት ነው፡፡

ግብርና

“ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ ነው። የወጪ ንግድ ገቢያችን ዋልታም ነው። በርካታ የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚሳተፍበት ነው። ይህም ትልቅ ስፍራ እንዲሰጠው ያደርጋል” በማለት የግብርናውን መስክ አስመልክቶ ማብራሪያ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ በዚህ ዘርፍ በዘንድሮው ዓመት 6 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንዲያመጣ ታቅዶ በትኩረት መሠራቱን ገልፀዋል፡፡ የግብርናው ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ልዩ ትኩረት ያገኘው “ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነት ማግኘት አለባት፤ አምርታ መብላት ያልቻለች ሀገር ብሔራዊ ጥቀሞቿን ለማረጋገጥ ትቸገራለች” በሚል የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ግብ ተይዞ በመሠራቱ ነው” ብለዋል፡፡ በዚህም አመርቂ ውጤት እንደተመዘገበ ተናግረዋል፡፡

አክለው እንዳስረዱት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት 27 ሚሊዮን በምግብ ዋስትና (በሴፍቲኔት) ተይዘው የነበሩ ዜጎች ከሴፍቲኔት ለማሸጋገር ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም ለረጅም ዘመናት በሴፍቲኔት ሲተዳደሩ የነበሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ወደመተዳደር ተሸጋግረዋል። 23 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ከሴፍቲኔት ተረጂነት ነጻ ወጥተዋል። ይህ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ስለሆነ ኩራት ሊሰማን ይገባል። ቀሪው ከ4 ሚሊዮን ያላነሰ ተረጂም ነጻ በማውጣት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠች ሀገር ማድረግ አለብን።

ሰፊ የሚታረስ መሬት ያላትን ሀገር በግብርና ምርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚሠራውን ሥራ አጋዥ የሚሆን የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀመር እና ከ40 ወራት በኋላ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪ

በ2017 በጀት ዓመት በኢንዱስትሪው ዘርፍ 12 ከመቶ የሚሆን ዕድገት ለማስመዝገብ እንደሀገር ታቅዶ እየተሠራ መቆየቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዘርፍ አመርቂ ውጤት መታየቱንም ጠቁመዋል፡፡ በተለይ “የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ” ለኢንዱስትሪው መስክ ዕድገት ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታምርት የማምረት አቅም አምና ከነበረበት 59 ከመቶ ዘንድሮ ወደ 65 በመቶ ደርሷል። ይህም የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ የተገኘ ነው ሲሉም አክለዋል።

የሲሚንቶ ምርት ከፍ ብሏል። በብረት ምርት ውጤቶች 18 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል። ኢትዮጵያ ብረት የማምረት አቅም ገንብታለች። የብረት ፍላጎትን ሙሉ ለሙሉ ማሟላት የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል። በዓመት 600 ሺህ ቶን ገደማ የመስታወት ምርት የሚያመርት ፋብሪካ እየተገነባ ይገኛል። የፋብሪካው ሥራ በሚቀጥለው ታህሳስ ወይም ጥር ላይ ይጠናቀቃል። የሶላር ምርት ፓናል ምርት የሚያመርቱ ፋብርካዎችም እየተገነቡ ነው፡፡ በቅርቡ ይመረቃሉ። ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ የማዕድን እና ጋዝ ምርትን ለመጠቀም ተስፋ ሰጪ ተግባራትን እየሠራች እና ተጠቃሚነቷን እያረጋገጠች ስለመሆኑ በሰጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ትላልቅ የማዕድን አቅም ካላቸው ሀገራት አንዷ ናት፡፡ እስካሁን የትኩረት፣ የአመራር እና የዕይታ ማነስ ስለነበረ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማገዝ ሳይችል ቆይቷል፡፡ አሁን እያነቃቃነው ነው፡፡ በዚህ ዓመት 37 ቶን ወርቅ ወደ ውጭ ተልኳል። ይህ በየትኛውም ዘመን ያልነበረ ስኬት ነው። ሌላው ጋዝ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የጋዝ ምርት በቅርቡ ለገበያ ማቅረብ ትጀምራለች። በዚህም ሠርቶ አዳሪ እንጂ አውርቶ አዳሪ አለመሆናችንን በተከታታይ እያሳየን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡

አገልግሎት

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የአገልግሎት ዘርፉ 8 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ይህ ዘርፍ በተቀናጀ መንገድ ከተሠራበት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመሸከም ያለው ጉልበት ከፍተኛ ነው። ዘርፉ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የንግድ አገልግሎቶችን እና ቴክኖሎጂን ያካትታል። ዘንድሮ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኹነቶች በኢትዮጵያ ተስተናግደዋል። 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የውጭ ጎብኝዎች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል።

የኮሪደር ልማቱ፣ የመስህብ ስፍራዎች ግንባታ፣ አንድነት ፓርክ፣ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት፣ ሣይንስ ሙዚየም፣ ወዳጅነት ፓርክ ለጎብኚዎች ቁጥር መጨመር ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ለዘርፉ ማደግ ወሳኝ አስተዋፅኦ የሚያደርገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ ዓመት ብቻ 13 አዳዲስ አውሮፕላን ገዝቷል፡፡ ስድስት አዳዲስ መዳረሻዎችን ጨምሯል፡፡ ከ19 ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን አጓጉዟል፡፡ የባቡር አገልግሎትም ወጪና ገቢ ንግድ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

የወጭ ንግድ እና የፋይናንስ ዘርፍ

የወጭ ንግድ እና የፋይናንስ ዘርፍ ላይ በ2017 በጀት ዓመት የታየው ለውጥ እና ዕድገት አበረታች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ጠቁመዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ በዚህ ዓመት ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 8 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ተሳክቷል፡፡ ይህም ከዕቅዱ የ3 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ እንዲሁም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ከእጥፍ በላይ ዕድገት አስመዝግቧል። በተጨማሪም፤ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ውስጥ ከሚልኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) 7 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዮን ዶላር፣ ከአገልግሎት 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል። አምና ከብድርና እርዳታ ውጭ ያሉትን የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገዶችን በመጠቀም የተገኘው ገንዘብ 24 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዘንድሮ ይህ ወደ 32 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። ይህም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤት ማሳያ ነው።

አክለው እንዳብራሩት፤ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርሙ በዚህ ዓመት አዎንታዊና ጤናማ ዕድገት አስመዝግቧል። የፋይናንስ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እና የቨርችዋል ግብይት በከፍተኛ መጠን እያደገ ነው። የዲጅታል ግብይት 12 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ከጥሬ ገንዘብ ግብይቱ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ብልጫ አለው። 24 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በቨርቹዋል ብድር ተደራሽ ተደርጓል። በአጠቃላይ በዓመቱ የታቀደው 8 ነጥብ 4 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደሚሳካ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በአገልግሎትና ሌሎችም ዘርፎች የተገኙ  ውጤቶች አመላካች ናቸው።

ገቢ እና ዕዳ

የገቢ ምጣኔን ለማሳደግ እና የዕዳ ቅነሳን በውጤታማነት ለመፈፀም የተሠራውን ሥራ እና የተመዘገበውን ውጤት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ እንደገለፁት፤  ዘንድሮ 900 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡ አጠቃላይ ወጪ ደግሞ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ነው። የ300 ቢሊዮን ብር ልዩነት አለው። ገቢው ከአጠቃላይ ጥቅል ምርት አንፃር ምጣኔው በጣም ዝቅተኛ ነው። 46 ሺህ የሚጠጉ የታክስ ተመዝጋቢዎች ግብር እየከፈሉ አይደለም። ከፊሉ የኪሳራ ሪፖርት በማቅረብ፣ ከፊሉ ‘ገቢና ወጪው ተመጣጣኝ ነው፤ ትርፍ የለኝም’ በማለት ከፊሉ ደግሞ ሪፖርት የማያቀርብ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ንግድ ፈቃድ ከወሰዱት መካከል ግብር እየከፈሉ ያሉት 37 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ከእነዚህም የሚሰበሰበው ገቢ ከአጠቃላዩ 60 በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ነው። 40 በመቶውን ገቢ ከተለያዩ ምንጮች ነው የሚገኘው።

አያይዘው እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ 37 በመቶ ብቻ የሆነውን የግብር ከፋይ ቁጥር 50 በመቶ እንኳን ማድረስ ከተቻለ ከታክስ የሚሰበሰበው ገቢ ይጨምራል። የታክስ አስተዳደራችንን ችግር ለማስተካከል ሪፎርም እየተደረገ ነው፤ ግብር ስወራን ማስቀረት አለብን። ኢ-መደበኛ የደረሰኝ ጉዳዮችን ማስተካከል አለብን። ግብር አከፋፈልን ዲጅታላይዝ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራትም ውጤት እያመጡ ነው። ግብር ከፋዮች በታማኝነት ግብር መክፈል ካልቻሉ መንገድ፣ ውሃ፣ ትምህርት በጥቅሉ ሀገር የለም ማለት ነው። ይህን ታሳቢ በማድረግም የንግዱ ማህበረሰብ ግብራቸውን በታማኝነት ሊከፍሉ ይገባል።

ዕዳን ለመክፈል በተያዘው ዕቅድ መሰረት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ መዋሉን ባስረዱበት ማብራሪያቸው፤ “በዚህ ዓመት 92 ቢሊዮን ብር ዕዳ ከፍለናል። ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድም የንግድ ብድር አልተወሰደም። ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል። የዕዳ ሽግሽጉ ትናንት በፈረንሳይ የመጨረሻውን ስምምነት ገንዘብ ሚኒስቴር ተፈራርሟል። በዚህም 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር ከዚህ ቀደም በነበሩት መንግስታት የተበደሩትን ዕዳ በማሸጋሸግ የኢትዮጵያን የዕዳ ቀንበር ማንሳት ችለናል” ብለዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት

የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ዋነኛ መፍትሔው ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶር)፤ መንግስት ለችግሩ ዘላቂና ሁነኛ መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህንን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ብድር ሳይወሰድ ዓመቱን ሙሉ ማጠናቀቁ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲ፣ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያ፣ በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ከፍተኛ ድጎማ መደረጉ፣ ምርትንና ገበያን በቀጥታ ማገናኘት መቻሉ ትልቅ ውጤት እንዲመጣ አስችለዋል። የዋጋ ግሽበቱ በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩ ዜጎች ላይ ከፍትኛ ጫና እንዳያሳድር 350 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል። የዋጋ ግሽበቱ ከሁለት አሃዝ ወደ ነጠላ አሃዝ መውረድ አለበት። የዋጋ ግሽበትን ከፍላጎት ጋር ማጣጣም የሚቻለው የእያንዳንዱን ሰው ገቢ ማሳደግ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አጠቃላይ ሀገራዊ እድገትን ማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው። መፍትሔውም ፈተናዎችን በጋራ ተቋቁሞ መሥራት ነው ብለዋል።

በጋዜጣዋ ሪፖርተሮች

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review