AMN – የካቲት 17/2017 ዓ.ም
ከየካቲት 7 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 236.8 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 18 ሚሊየን ብር የወጭ፣ በድምሩ 254.8 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች ፣ መድኃኒት፣ የቁም እንስሳት እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች እንደሚገኙበትም አመላክቷል፡፡
በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዲስ አበባ ኤርፖርት፣ ሞያሌ እና አዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ፣ በቅደም ተከተላቸውም 51 ሚሊየን፣ 50 ሚሊየን እና 25 ሚሊየን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላት እና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ እና በበረራ የተያዙ ሲሆን፣ የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 17 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እና ስምንት ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች እና አመራሮች፣ የክልል እና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝብ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ ማቅረቡን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡