28ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የድንበር አስተዳዳሪዎች እና ኮሚሽነሮች የጋራ ስብሰባ ተጀመረ

AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም

28ኛው የኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የጋራ ድንበር አስተዳዳሪዎች እና ኮሚሽነሮች የጋራ ስብሰባ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

28ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የድንበር አስተዳዳሪዎች እና ኮሚሽነሮች የጋራ ስብሰባ ልዑክ መሪ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት፣ የኢትዮ-ጅቡቲ ግንኙነት ከጋራ ድንበር አስተዳደር ባለፈ በደም የተሳሰረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አገራቱ ያላቸው የኢኮኖሚ ፣ ማህበራዊ እና ደህንነትን በማስከበር የጋራ ግንኙነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አውስተዋል።

ወ/ሮ ሰላማዊት ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በኢጋድ በማዕቀፍ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ጉልህ መሆኑን ጠቁመው ፤ ሁለቱ አገራት በተለያዩ ዘርፎች በኤሌክትሪክ ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በንግድ እረጅም ዘመን ያስቆጠረ ጠንካራ ግንኘነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የጅቡቲ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ጸሃፊ ሱሉማን ሙአሚን በበኩላቸው፣ የኢትዮ ጅቡቲን መልካም ግንኙነት ወደፊት ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰራ በመግለፅ በድንበር ጉዳዮች ላይ በተለይም የጋራ መሰረተ ልማትን በትብብር በማጠናከር የጋራ ራዕያችንን እንደምናሳካ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡

ዋና ጸሃፊው የሀገራቱ ግብ እና ራዕይ ተመሳሳይ በመሆኑ በሰላም እና ደህንነት በጋራ በመሆን ልማታችንን በማሳደግ ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላማዊት በሀገራቱ ድንበር አካባቢ የሚስተዋሉ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣የሽብር እንቅስቃሴዎች እና ህገ ወጥ ንግድን በጋራ በመከላከል እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ጥቅም እንዲጠበቅ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት ቆይታ የሚያደርገው ስብሰባ የድንበር አስተዳደር፣ የንግድ ግንኙነት እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር ላይ ትኩረቱን በማድረግ ውይይቱ ይካሄዳል ።

በስብሰባው የሁለቱ አገራት የመከላከያ፤የንግድ የፀጥታ እና ደህንነት ፖሊስ የኢሚግሬሽን ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review