2ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል ብዝሃ-ማንነታችንን ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል- ተሳታፊዎች

You are currently viewing 2ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል ብዝሃ-ማንነታችንን ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል- ተሳታፊዎች

AMN- መጋቢት 14/2017 ዓ.ም

2ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል ብዝሃ-ማንነታችንን ለማስተዋወቅ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ በምስራቅ አፍሪካ የኪነ ጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል የተሳተፉ ልዑካን ቡድን ገለጹ፡፡

ፌስቲቫሉ “ጥበብና ባህል ለቀጣናዊ ትብብር ” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሔድ ከጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

በፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ፣ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ፣ ሩዋንዳ፣ የደቡብ ሱዳን፣ የኡጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጎንጎ እና የቡሩንዲ የኪነ-ጥበባት እና ባህል ልዑካን ቡድን የየአገሮቻቸውን ባህሎች አሳይተዋል፡፡

ኢዜአ ካነጋገራቸው የሀገራት ሉዑካን ቡድን መካከል ከኡጋንዳ ኦቶ ሉሲ፣ ይህ የኪነ ጥበብ እና ባህል ፌስቲቫል እንደ ምሥራቅ አፍሪካ ለእርስ በእርስ ትውውቅ በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ኪነ-ጥበባት እና ባህል የሰላም፣ የልማት፣ የእድገት እና የለውጥ መሳሪያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀገራቸው ከ65 በላይ ብዝሃ-ማንነቶች ያሉ መሆናቸውን የጠቀሱት ኦቶ ሉሲ፣ እነዚህ ብዝሃ-ማንነቶች ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ሁለተኛው የምስራቅ አፍሪካ ፌስቲቫል ብዝሃ-ማንነታችንን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ መድረኩ ያሉንን ቅርሶች፣ ቋንቋዎች፣ ሙዚቃዎች፣ ውዝዋዜዎችና ሌሎች መሰል ብዝሃ ማንነቶችን ከምስራቅ አፍሪካ ባሻገር ለተቀረው አለም እንድናሳይ አድርጎናል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያ ሲዳማ ክልል ዳዊት ፈይሳ በበኩሉ፣ ፌስቲቫሉ ባህላችንን ለማስተዋወቅ እና ከቀጣናው ሀገራት ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር ይረዳናል ብሏል፡፡

መጀመሪያ ፌስቲቫሉ ባህላችንን እንድናስተዋውቅ እድል ፈጥሮልናል፣ ቀጥሎም ስላሉን ባህላዊ ምርቶች ግንዛቤ በመፍጠር ቀጣይነት ያለው የገበያ ትስስር እንድንፈጥር የሚያደርግ መሆኑን ነው የተናገረው፡፡

በፌስቲቫሉ ምስራቅ አፍሪካ ምን ያክል የኪነ ጥበባት እና የባህል ባለጸጋ መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ ያለችው ደግሞ ከቡርንደ ኤሚ ቢታሎ ናት፡፡

ስለሆነም ፌስቲቫሉ አንዳችን የሌላኛችንን ማንነት እንድናውቅ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር የቀጣናውን ሀገራት በሰላምና በልማት ለማስተሳሰር ትልቅ እድል እንዳለው ገልጻለች፡፡

በርካታ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ያሳተፈው 2ኛው የምስራቅ አፍሪካ የኪነ-ጥበባት እና ባህል ፌስቲቫል ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review