AMN – የካቲት 28/2017 ዓ.ም
2ኛው የጆርካ አዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና ውድድር ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 6 /2017 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በአመቱ ውስጥ ከሚያዘጋጀው ውድድሮች ውስጥ አንዱ የሆነው ይህ የክለቦች አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ክለቦች ራሳቸውን የሚመዝኑበት እንደሆነም ተገልጿል።
ውድድሩ አትሌቶችም አቋማቸውን የሚፈትሹበት እንደሆነ የገለፁት የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አትሌት መልካሙ ተገኜ፣ ታዳጊዎች ላይም ወርደን እየሰራን እንገኛለን ብሏል።

ይህ ውድድር በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና በአለም አቀፍ ውድድሮች ተወዳዳሪ የሆኑ አትሌቶች የሚገኙበት መሆኑም የተገለፀ ሲሆን ከ3 ወርቅ በላይ የሚያመጡ አትሌቶች እና ክብረወሰን ለሚያሻሽሉ አትሌቶች ልዩ የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱን የጆርካ ኢቨንት ተወካይ አቶ ተሾመ በቀለ ተናግረዋል።
ከ100 ሜትር እስከ 10ሺ ሜትር በሚካሄደው ውድድር ከ829 በላይ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን የፖሊስ ውድድር ላይ የሚገኙት ኦሜድላ እና አዲስ አበባ ፖሊስም እስከ ሰኞ ድረስ ይቀላቀላሉ ተብሏል።
6 የአንደኛ ዲቪዚዮን እና 11 የ2ኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን በውድድሩ ቦታ የዶፒንግ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና ምርመራ እንደሚደረግም ተገልጿል።
በአልማዝ አዳነ