ሶስተኛው ምዕራፍ የዓለም አቀፉ የጁገል ቅርስ የኮሪደር መልሶ ልማት እና ጥበቃ ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድር፣ በዓለም አቀፉ የጁገል ቅርስ ሶስተኛ ምዕራፍ የተጀመረውን የኮሪደር መልሶ ልማት ስራ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታውም፣ ብዝሃ ኢኮኖሚን ለመገንባት እንዲያስችሉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ በመተግበር ላይ ካሉ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አውታሮች መካከል ቱሪዝም አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንን መሰረት ባደረገ መልኩ በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውንም ጠቁመዋል።
በተለይም ካሁን ቀደም ለቅርሱ ከመንግስት በጀት ሳይያዝለት በተቋማት እና ህብረተሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ የቅርስ ጥገናና ልማት ስራዎች አበረታች ውጤቶችን አስገኝተዋል ብለዋል።
ቀደም ብለው ከተሰሩ ስራዎች ልምድ በመውሰድ ሶስተኛው ምዕራፍ የቅርስ ልማትና ጥበቃ ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
በሶስተኛው ምዕራፍ የጁገል መልሶ ማልማት ስራም መንገዶችን በአካባቢው የሚገኙ ጥርብ የድንጋይ ሀብትን በመጠቀም የማስዋብ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል ብለዋል።
የተጀመሩ የቅርስ ጥበቃ ስራዎች የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም ገቢ ለማመንጨት የሚያግዙ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አክለዋል።
በመልሶ ማልማት ስራው የአካባቢውን ማህበረሰብ በተለይ ወጣቱን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱንም ገልፀዋል።
የተጀመረውን የመልሶ ማልማት ስራ በጥራት እና ፍጥነት በተያዘለት ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ የሐረሪ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ሱልጣን አብዱሰላም ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች መገኘታቸውን የክልሉ መረጃ ያመለክታል።