AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም
የግብርና ሚኒስቴር እና AJJDC (American Jewish Joint Distribution Committee) በኢትዮጵያ የሆርቲካልቸር ምርታማነትን መጨመር የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
48 ሚሊዮን ብር የተበጀተለት ፕሮጀክቱ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 3 ሺህ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ ዋና አላማ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶአደሮች የተሻሻሉ ዝርያዎችን እንዲያለሙ ድጋፍ በማድረግ እና የመስኖ ውሃ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነትን በማሳደግ ኑሯቸው እንዲሻሻል ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
በስምምነት ስነ-ስርዓቱ ላይ በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ የአርሶ አደሩን ምርታማነት እንደሚያሻሽል እና የኑሮ ሁኔታቸውን በመቀየር ስራውን ለማስፋት ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡
የAJJDC የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ፈገግታ ለማ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከዚህ ቀደም በሰሩባቸው ክልሎች ያገኙትን መልካም ተሞክሮዎች በማስፋት በቀጣይ በዘጠኝ ክልሎች ላይ ለመስራት ከግብርና ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡