30 ሺህ መኪኖችን ማስተናገድ የሚችለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ

You are currently viewing 30 ሺህ መኪኖችን ማስተናገድ የሚችለው የመኪና ማቆሚያ ስፍራ

AMN- ሰኔ 03/2017 ዓ.ም

መርሴዲስ ቤንዝ ባካሄደው ጥናት መሰረት 40 በመቶ የሚሆኑ የመኪና አደጋዎች በመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ይከሰታሉ፡፡

ከነዚህ አደጋዎች መካከልም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ከመኪና ማቆሚያ ቦታዎች ለመውጣት በሚደረጉ ጥረቶች፣ በተለይም ወደኋላ በማሽከርከር ጊዜ እንደሚፈጠሩ ጥናቱ ያመላክታል፡፡

እንደነዚህ አይነት ዳሰሳዎች በከፍተኛ ጥናት የሚሰሩ እና በቴክኖሎጂ የታገዙ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች አስፈላጊነትን አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው፡፡

በተለይም በትላልቅ ከተሞች እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር እና የተሽከርካሪ ባለቤትነት መጨመር አንፃር የመኪና ማቆሚያዎች እጥረት የሚስተዋል ነው፡፡

ይህን ለመቅረፍም የዓለም ከተሞች ትላልቅ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን የሚገነቡ ሲሆን፣ ከነዚህ ከተሞች አንዷ የካናዳዋ ኤድመንተን ከተማ ናት፡፡

በኤድመንተን አልበርታ የሚገኘው የዌስት ኤድመንተን የገበያ እና የመዝናኛ አዳራሽ ፓርኪንግ በዓለም ትልቁ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ሆኖ በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ሰፍሯል፡፡

የመኪና ማቆሚያው 20 ሺህ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ዋና የመኪና ማቆሚያ ስፍራ እንዲሁም በተጨናነቁ ጊዜያት 10 ሺህ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ለማስቆም የሚያገለግል ቦታ አለው፡፡

በካናዳ 2ኛው እንቅስቃሴ የሚበዛበት የገበያ ማዕከል በሆነው የዌስት ኤድመንተን የሚገኘው የመኪና ማቆሚያው በፈረንጆቹ 1981 አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ ከዛን ጊዜ ጀምሮ 20 ሺህ መኪኖችን ማስተናገድ የሚችል ትልቁ የመኪና ማቆሚያ በሚል በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ስሙ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review