AMN-የካቲት 04 /2017 ዓ.ም
302 የካሳንቺስ እና የደምበል አካባቢ የልማት ተነሺዎች በዛሬው እለት የመንግስት መኖሪያ ቤት እጣ በዛሬው እለት አውጥተዋል፡
በእጣ አወጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አዲሱ ሻንቆ፣ ለዜጎች የሚሰራ መንግስት በመኖሩ የልማት ተነሺዎች ምንም እንግልት ሳይደርስባቸው ወደተለዋጭ ቤታቸው እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት ለህዝቡ ያለውን ቀረቤታ ለልማት ተነሺዎች በሚያደርገው ድጋፍ አሳይቷል ያሉት ዶክተር አዲሱ የዛሬው ባለእድለኞችም ምንም እንግልት ሳይደርስባቸው መጓጓዣ ጭምር በመመደብ ወደ አዲሱ ቤታቸው ይገባሉ ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በልማቱ ተነስተው በተለያዩ አካባቢዎች የመኖሪያ ቤት የተሰጣቸውን ነዋሪዎችን ሄደው መጎብኘታቸውን የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው በዚህ እጣም በተመሳሳይ ነዋሪዎቹ ካላቸው የጋራ የኑሮ ዘይቤ ላለመለየት በአንድ አካባቢ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ባለ አንድ እና ባለ ሁለት መኝታ በአጠቃላይ 302 የመንግስት የመኖሪያ ቤቶች በቦሌ ባሻሌ፣ በሀያት 1 እና 2 ሳይት የመኖሪያ መንደሮች ለባለእድለኞች በእጣቸው መሰረት ተደራሽ መደረጉን ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡