AMN – የካቲት 11/2017 ዓ.ም
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ሀገራዊ ጥቅሞችን ማፅናትና የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ መድረኮች በብቃት ማስተናገድ እንደምትችል ያረጋገጠችበት እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጉባዔው ዝግጅት ብሄራዊ ኮሚቴ ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በጉባዔው መጠናቀቅና ሀገራዊ ትሩፋቶች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ለአንድ ዓመት ያክል በብሄራዊ ደረጃ ሰፊ ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ በሁሉም ረገድ የተሳካ ሆኖ ስለመቀጠናቀቁ ሚኒስትር ዴዔታዋ አስታውቀዋል።
አንድ ንጉስ ፣ 30 ርዕሳነ ብሄሮች ፣ ሶስት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ፣ አምስት ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ጨምሮ የርካታ ሀገራት ከፍተኛ ልዑካን ቡድን አባላት የተገኙበት ጉባዔው የሀገርን ከፍታ ፣ የአዲስ አበባን አሁናዊ ገፅታ አጉልቶ ማሳየት ያስቻለም ነበር ብለዋል።
ጉባዔው ከዚህ ቀደም ከነበሩ ጉባኤዎች በተሻለ መልኩ የተሳካ ሆኖ ከመጠናቀቁም ባሻገር ሀገራዊ ጥቅሞችን ማረጋገጥ ፣ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ በሚገባ ማጉላት የተቻለበት ነበርም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታዋ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧን ያወሱት አምባሳደር ብርቱካን ይህም የኢትዮጵያን ለአህጉራዊ ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ድርሻ ዋጋ የሰጠ ለበለጠ ሀላፊነትም ዕድል የሰጠ ስለመሆኑ ገልፀዋል።
ከዚህ ባሻገርም ከጉባዔዉ ጎን ለጎን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) ጨምሮ የተደረጉ የጎንዮሽ ምክክሮች ሀገራዊ ጥቅም ማረጋገጥ ያስቻሉ ስምምነትና መግባባቶች የተደረሱባቸው መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ከሁሉም በላይ የዘንድሮው ጉባዔ ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ የሁነትና ስብሰባ ማስተናገጃ ማዕከላትን የገነባቸው አዲስ አበባ መሰል አህጉራዊ ከፍ ሲልም ዓለም አቀፍ መድረኮችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ያሳየችበት ነበርም ብለዋል ሚኒስትር ዴዔታዋ።
ለጉባዔው መሳካት ሀላፊነታቸውን ለተወጡና ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ሚኒስትር ዴዔታዋ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአቡ ቻሌ

All reactions:
32Tsehhay Habte and 31 others