AMN – የካቲት 10/2017 ዓ.ም
የህብረቱ ጉባኤ ለከተማችን ድምቀትና የኢኮኖሚ መነቃቃት ከመፍጠሩ ባሻገር የቱሪዝም መስህቦችን እና የከተማችንን መልካም ገጽታዎችን እንዲሁም የህዝባችንን ጨዋነትና እንግዳ ተቀባይነት በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ በዚህ በ38ኛው የመሪዎች ጉባኤ አዲስ አበባ እንደወትሮው ሁሉ እንግዳ ተቀባይነትና ያለባትን ተደራራቢ ሃላፊነት ስራው ከሚመለከታቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶች እና ከከተማችን ነዋሪዎችም ጋር በመሆን ላቅ ያለ የማስተናገድ ብቃትን ያሳየችበት ሲሆን ተባብረን በጋራ በሰራነዉ ስራ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ወንድሞች እና እህቶቻችን ኩራት መሆናችንን ዳግም አሳይተናል ብለዋል።

እንግዶቻችንም ባዩት ለዉጥ እየተደነቁ፣ በአዲስ አበባ መቆየት እየወደዱ እና ደግመው ደጋግመዉ መምጣትን እየተመኙ መሆኑን መስማታቸውንም አንስተዋል።
የከተማችን ነዋሪዎችም ላሳያችሁት ታላቅ እንግዳ አክባሪነትና ተቀባይነት፣ እንዲሁም እንግዶችን ለማስተናገድ ዓላማ መንገዶች ሲዘጉ ፍጹም ትዕግስት እና ጨዋነታችሁ ላቅ ያለ ምስጋናዬን ላቀርብላችሁ እወዳለሁ ብለዋል።