38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቅቋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- የካቲት 10/2017 ዓ.ም

38ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት ፣ ኢትዮጵያም እንደ ኅብረቱ መቀመጫ ሀገር የሚጠበቅባትን ማከናወኗን ገልጸዋል።

አቀባበሉ፣ መስተንግዶውና መርሐ ግብሮቹ እንግዶቻችንን ያስደመመ ነበር ብለዋል።

እንግዶቿ የማይረሳ ትውስታ፣ የማያረጅ ትዝታ እንዲኖራቸው አድርጋለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ የተነሣ የቆይታ ጊዜያቸውን ያራዘሙ እንግዶች ብዙ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ለኅብረቱ ዓላማዎች እና መርሖች መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት በጉባኤው ዝግጅትና መስተንግዶ በተግባር ማሳየቷን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲከናወን ብዙዎች የሚቻላቸውን ሁሉ ማድረጋቸውንም አውስተዋል።

አዘጋጅ ኮሚቴው፣ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማቶች፣ የፕሮቶኮል ባለሞያዎች፣ የቴሌና የመብራት ተቋማት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የትራፊክ ፖሊሶች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ሚዲያዎች፣ የኪነ ጥበብና የሰርከስ አባላት፣ ሆቴሎች፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር የሥራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች፣ የጽዳት ባለሞያዎች፣ እንደ አንድ ልብ ሰሚ፣ እንደ አንድ አካል ፈጻሚ ሆነው መስራታቸውን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ለእንግዶቹ ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት፣ መንገዶች ሲዘጉ በትዕግሥት በመጠባበቅ፣ ለጉባኤው ስኬት የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጓል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁሉም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በራሳቸው ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

ሁላችንም በሀገር ፍቅር ስሜት በሥርዓት እና በዲሲፕሊን በመሥራታችን እንግዶቻችንን አስደምመናል ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

‘ የሀገራችንን ከፍታ አሳይተናል። ከአንድ ሺ በላይ የሚሆኑት የሚዲያ ሰዎች መልካም ገጽታችንን ለዓለም አሳይተዋል። ከዐሥር ሺ ዎች የሚልቁት እንግዶች እየበለጸገች ስለምትገኘው ሀገራችን ምስክሮች ሆነዋል’ ሲሉም ገልጸዋል።

ይህ ትብብራችንና ለሀገራችን ስኬት ያለን ቁርጠኝነት፣ ከጉባኤው በኋላም እንደሚቀጥል አምናለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት መሆንዋ በዐለት ላይ እስኪጻፍ ድረስ ጥረታችን ይቀጥላል’ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review