40 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ማለት ቢያንስ 40 ቢሊዮን ዶላር ለልጆቻችን ኢንቨስት ማድረግ ማለት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing 40 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ማለት ቢያንስ 40 ቢሊዮን ዶላር ለልጆቻችን ኢንቨስት ማድረግ ማለት ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተገኝተው አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርኃግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በቂ ሀብት ሳንይዝ ህዝብን ተማምነን በጀመርነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃግብር በ4 ዓመት ውስጥ ከእቅዳችን በላይ አሳክተናል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም 39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ገደማ ችግኞች የተተከሉ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከዛሬው ተከላ ጋር ከ40 ቢሊየን ያላነሱ ችግኞች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚተከልበት ዓመት ይሆናል ብለዋል።

40 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ማለት ቢያንስ 40 ቢሊዮን ዶላር ለልጆቻችን ኢንቨስት አደረግን ማለት ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።ይህም ወደፊት መጪው ትውልድ በበለጠ አቅም እና ውጤት የሚጠቀምበት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

እንደ ሀገር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን እያሰብን የምናደርገው ኢንቨስትመንት ኢትዮጵያ የበለጸገችና ሉዓላዊነቷን በሁሉም መስክ የምታረጋግጥ ያደርጋታል ብለዋል።

“ዛሬ የምትተክሉ እጆች የተባረካችሁ እና ለልጆቻችሁ መሰረት የምትጥሉ ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኝ እተክላለው ስትል በህዝበ ያላትን መተማመንና በመደመር ያለውን ጉልበት ባለፉት ዓመታት በተግባር ፈትሻ ስላየች ነው ብለዋል።

ዛሬ በሁሉም የስራ መስክ ያሉ ዜጎች ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የማይቻልን የምትችል ያሰበችውን የምታሳካ እንዲሁም ጀምሮ መጨረስ የምትችል ሀገር መሆኗን ለዓለም የሚያሳዩበት ዕለት ነው ብለዋል።

“600 ሚለዮን መተከሉን እስክናረጋግጥ ድረስ ሙሉ ቀን እንተክላለን ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው ኢትዮጵያዊያን  ባሉበት ስፍራ ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ እንድትሆን እንስራ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በሰፊና ሁሴን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review