AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
ዓመታዊው የጥቅምት አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ በመንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በዛሬው ዕለት የተጀመረ ሲሆን፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ጉባኤውን በጸሎት አስጀምረዋል።
በጠቅላላ ጉባኤው የመክፈቻ ንግግራቸውም ሹመት እስካለ ድረስ ተጠያቂነትም አለው ብለዋል።
ሹመት የመፈጸሚያና የማስፈጸሚያ ህጋዊ መሳሪያ ነው ያሉት ፓትሪያርኩ፤ ሹመትን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ለጥፋት ሊውል ይችላል ተጠያቂነትንም ያስከትላል ሲሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ለተመደብንበት ተልዕኮ በጽናት መቆምና በትጋት ማገልገል ይገባል በማለት አስገንዝበዋል።
ባለንበት ዘመን በታማኝነት መቆምና ምዕመኑን በትጋት ማገልገል ይጠበቅብናል ያሉት ብጹዕነታቸው፤ ቤተክርስቲያኒቱ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ልትደርስበት አቅዳ እየሰራችው ላለው ተልዕኮ ስኬታማነት ሁሉም በየደረጃው በትጋት መስራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
በምትኩ ተሾመ