
AMN – ታኅሣሥ 9 /2017 ዓ.ም
በቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ጉድጓድ ውስጥ ለውስጥ 2 ኪሎ ሜትር በመጓዝ 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮፐር ወይም መዳብ ሰርቀዋል የተባሉ 5 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገለፀ።
ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ጉምሩክ ጀርባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት ግቢ ውስጥ ነው።
ግለሰቦቹ ጥናት በማድረግ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ይህን ወንጀል እንደሚፈፅሙ ከአካባቢው የጥበቃ ሰራተኞች መረጃ እንደደረሰው ከክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ፖሊስ የደረሰውን መረጃውን መነሻ በማድረግ በወንጀል ቦታው ላይ ባደረገው ጥናት ንብረትነቱ የጉምሩክ ኮሚሽን የሆነ በተለያዩ ኮንቴይነሮች ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ማስቀመጡን እና ወንጀል ሲፈፀምባቸው እንደነበር አረጋግጧል ።
ፖሊስም ወንጀል መፈፀሙን ካረጋገጠ በኋላ ባደረገው የተጠናከረ ክትትል እነዚህ ተጠርጣሪዎች እንደተለመደው አፋ (ኦቼ) የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ አካባቢ ከሚገኘው የፍሳሽ ማስወገጃ ጉድጉዳ በመግባት እና 2 ኪሎ ሜትር ውስጥ ለውስጥ በመጓዝ የጉምሩክ ኮሚሽን አስቀምጧቸው ከነበሩ ኮንቴይነሮች አንደኛውን በመክፈት 500 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮፐር ወይም መዳብ ይዘው በፍሳሽ ማስወገጃው ጉድጓድ ሲወጡ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።
እነዚህን ተጠርጣሪዎች በመያዛቸው ኮንቴይነሩ ውስጥ የነበረ 5000 ኪሎግራም መዳብ ከዘረፋ ማትረፉን ፖሊስ አስታውቆ ተቋማትም ሆኑ ድርጅቶች ንብረቶቻቸው እንዳይሰረቁባቸው ጥበቃቸውን ከማጠናከር ባሻገር ቁጥጥር እና ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ በመረጃው አሳስቧል ።