የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እስካሁን ምን አሳየን?

AMN-መስከረም 11/2019 ዓ.ም

የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የአምስት ሳምንት መርሃግብር ካከናወነ በኋላ ለሀገራት ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ተቋርጧል። ቢቢሲ ስፖርትም ሊጉ እስካሁን ምን አሳየን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ የተወሰኑ ነጥቦችን ዘርዝሯል።

👉 አርሰናል መሸነፍ የሚችል ቡድን መሆኑን አሳይቷል

ከ22 ዓመት ቆይታ በኋላ ባለፈው የውድድር ዘመን የሊጉን ዋንጫ ያነሳው አርሰናል ዘንድሮም በጥሩ ብቃት ጀምሯል። በርካቶች ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት እንደገመቱት ከ91 ዓመታት በኋላ በተከታታይ የሊጉን ዋንጫ የሚያነሳም መስሎ ነበር።

የሚኬል አርቴታው ቡድን በሁሉም ውድድሮች ስምንት ጨዋታዎች አድርጎ ስምንቱንም በማሸነፍ ከዚህ ቀደም ይዞት የነበረውን ክብረወሰ ተጋርቶ ነው የጀመረው። ቡድኑ መሸነፍ አይደለም ግብም በቀላሉ የሚቆጠርበት አለመሆኑን አሳይቷል። በስምንቱ ጨዋታዎች የተቆጠረበት ሦስት ግብ ብቻ ነው።

በ5ኛ ሳምንት የሊግ መርሃግብሩ በብራይተን ብልጫ ተወስዶበት 3ለ0 መሸነፉ ግን ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል። ቡድኑ መሸነፍ እንደሚችልም አሳይቷል።

በእርግጥ ይህ አንድ ጨዋታ ብቻ ነው። በርካቶችን ያስገረመው የተቆተረበት ግብ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አርሰናል ሦስት ግቦች ተቆጥረውበት ሲሸነፍ ከጥቅምት 2024 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

👉 የኢንዞ ማሬስካ የተሳካ አጀማመር

በርካቶች ታላቁ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ሲቲን ሲለቅ ክለቡ መቸገሩ አይቀርም የሚል ግምት አስቀምጠዋል። በተለይ በኮሚኒቲ ሺልድ በአርሰናል 3ለ0 ሲሸነፍ ግምቱ እውን የሚሆን ይመስል ነበር።

ነገር ግን የፔፕ ጋርዲዮላ ረዳት በመሆን የሰራው ጣልያናዊው አሰልጣኝ ሊጉ ሲጀመር የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል። ያደረጋቸውን አምስት የሊግ ጨዋታዎችን ያሸነፈ ብቸኛው ቡድን በመሆንም ከአርሰናል በሦስት ነጥብ በልጦ የደረጃ ሰንጠረዡን እየመራ ይገኛል።

ያከናወናቸው የጨዋታ ብዛቶች ሙሉ ግምገማ ለማድረግ ቢከብድም ማንችስተር ሲቲ በርካቶች እንደገመቱት ላይቸገር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።

👉 የብራይተን እና ብሬንትፎርድ አስደናቂ ጅማሮ

ብራይተን እና ብሬንትፎርድ በታሪካቸው ታላላቅ ዋንጫዎችን አሸንፈው አያውቁም። የዘንድሮ አጀማመራቸው ግን ምናልት አንድ ነገር ሚያሳኩ አስመስሏቸዋል።

ብራይተን በአንድ ሳምንት ውስጥ ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናልን ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ አሸንፏል። በካራባኦ ካብ 3ኛ ዙር ዩናይትድን 3ለ2 ሲያሸንፍ ፤ በሊጉ 5ኛ ሳምንት ደግሞ አርሰናልን 3ለ0 ረቷል። የፋብያን ኸርዝለር ቡድን በሊጉ 10 ነጥብ በመያዝ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሽንፈት ካልቀመሱ ቡድኖች አንዱ የሆነው ብሬንትፎርድም በዘጠኝ ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በፕሪምየር ሊጉ 5ኛ ሳምንት ቼልሲን በግሩም ብቃት 3ለ0 ያሸነፈው ብሬንትፎርድ ለተጋጣሚዎቹ ፈተና መሆኑን ቀጥሏል። የኪት አንድሪውስ ቡድን በዚህ አቋሙ የአውሮፓ ውድድሮች ተሳትፎ የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ይመስላል።

👉 ጫና ውስጥ የገባው ማይክል ካሪክ

የማንችስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ገና ከአሁኑ ጫና ውስጥ ገብቷል። ሩበን አሞሪምን ተክቶ ጊዜያዊ የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ የጀመረው እንግሊዛዊው አሰልጣኝ የቻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎን ወደ ኦልድትራፎርድ ማምጣቱ በቋሚነት እንዲቀጠር አግዞታል።

ነገር ግን ቋሚ ከሆነ በኋላ አጀማመሩ ጥሩ አልሆነም። ከአምስት የሊግ ጨዋታዎች ያስመዘገበው አምስት ነጥብ ብቻ ነው።

ከካራባኦ ካፕ ውድድር ገና በጊዜ በብራይተን ተሸንፎ የወጣው ዩናይትድ ከሀገራት የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች በኋላ መሻሻል ካላሳየ ማይክል ካሪክ የመሰናበት እድሉ ሰፊ ይመስላል።

👉 የቶተንሃም አስደናጋጭ አጀማመር

በሮቤርቶ ዲ ዘርቢ የሚመራው ቶተንሃም ሆትስፐርስ በፕሪምየር ሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንድም ድል አላስመዘገበም። በሁለቱ አቻ ሲለያይ በሦስቱ ተሸንፏል። ቡድኑ ድል ማድረግ አይደለም ግብም ማስቆጠር ተስኖት ታይቷል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ በ5ኛ ሳምንት መርሃግብሩ በአስቶን ቪላ 3ለ2 ሲሸነፍ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የሊግ ግብ ያስመዘገበው። ከ300 ሚሊየን ፓውንድ በላይ ለዝውውር ያወጣው ቶተንሃም በዚህ ልክ ይቸገራል ተብሎ አልታሰበም። ዲ ዘርቢም በሚፈልገው መንገድ ጠንካራ ቡድን ይሰራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ነገሮች ግን የተገላቢጦሽ ሆነዋል። ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት በተመሳሳይ 17ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ቶትንሃም ብቃቱን ካላሻሻለ ከዚህም የከፋ ደረጃ ይጠብቀዋል። ቡድኑ አሁን ላይ ሁለት ነጥብ ብቻ ይዞ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review