ካይሮ ተረብሻለች፤ ሻዕቢያና ጽምዶም ተጨናንቀዋል

AMN- መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ግብጽ የሃገሬ ብሄራዊ ጥቅም የሚረጋገጠዉ የኢትዮጵን ሉዓላዊነትና ህልዉናን በመገዳደር እንዲሁም የሃገሪቱን ሠላምና ልማት በማደናቀፍ ነዉ የሚል እኩይ አላማ አላት።

ይህንን እኩይ አላማዋን የሚያስፈጽሙላት ደግሞ እንደ ሻዕቢያ፣ ህገወጡ የህወሃት ቡድንና ጽምዶ ያሉ ቅጥረኞች ናቸዉ።

የጥፋት ሃይሎቹ ከግብጽ በሚሰጣቸዉ ተልዕኮ፣ የበጀትና የቁሳቀስ ድጋፍ ላለፉት ስልሳና ሰባ አመታት የገዛ ሃገራቸዉን ለማፈራሰስ ሲታትሩ ኖረዋል።

በተለይ ሻዕቢያ ፈርዖኖቹን በታማኝነት የሚያገለግል የጥፋት መልዕክተኛ ሲሆን ለግብጽ ያለዉን ታማኝነት ለማረጋገጥ ኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል፣ ኢትዮጵያም የባህር በር እንድታጣ አድርጓል።

ሻዕቢያ ኢትዮጵያን የባህር በር አሳጥቶ ግብጾችን ከማስደሰትና የኢትዮጵያዊያንን የኑሮ ጫና ከማባባሱ በስተቀር የባህር በሩን ተጠቅሞ የገዛ ዜጎቹን ህይወት መለወጥም ሆነ ኤርትራን ማበልጸግ አልቻለም።

በሻዕቢያ ተጸንሶ በኤርትራ ምድር የተወለደዉ ህገወጡ የህወሃት ቡድንም ቢሆን የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ለማደናቀፍ ለሻዕቢያና ለፈርዖኖቹ በታማኝነት ከመላላክ ዉጭ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሠላምና ልማትን ማረጋጠጥ አልቻለም።

ቡድኑ ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የተቻለዉን ሁሉ ቢያደርግም የፈርዖኖቹን የጥፋት ተልዕኮ ማሳካት አልቻለም።

ሁለቱ ቅጥረኛ ሃይሎች በብሄር ስም የሚታገሉ ሌሎች ጽንፈኛ ሃይሎችን በማደራጀትና ጽምዶ የሚባል ጥምረት በመፍጠር በወንድማማች ህዝቦች መካከል በብሄርና በሃይማኖት ሽፋን የእርስ በርስ ግጭት ለመፍጠር ቢጥሩም መላዉ ኢትዮጵያዊያን ልዩነታቸዉን አክብረዉ አንድነታቸዉ በማጠናከር እኩይ ፍላጎታቸዉን ለማክሸፍ ችለዋል።

ቅጥረኞቹ የኢትዮጵያን የመልማትና የማደግ ራዕይ ለማደናቀፍ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን እና ፕሮጀክቶችን ለማዉደምና ለማቃጠል ቢሞክሩም በጀግናዉ የሃገር መከላከያ ሠራዊትና በሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ቆራጥ ተጋድሎና ጀግንነት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ማስቆም አልቻሉም።

ግብጽ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ከማድረግ አልፋ ብድርና ዕርዳታ እንዳታገኝ በርካታ ተጽእኖዎችን ብትፈጥርም ግድቡ ኃይል እንዳያመነጭ ማስቆም አልቻለችም።

ግብጽ እነዚህንና መሠል እኩይ ስልቶችን ተጠቅማ ኢትዮጵያን ለማዳከምና በቀጣናዉ ያላትን ተቀባይነት ይበልጥ ለማጠናከር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ብታፈስም እኩይ ፍላጎቷን ማሳካት አልቻለም።

ይልቁንም የለዉጡ መንግስት ይዞ የተነሳዉ ታላቋን ኢትዮጵያ የመገንባት እና ብልጽግናን የማረጋገጥ ራዕይ ለፈርዖኖቹ ትልቅ ስጋት ሆኗል።

ኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ያጣችዉን የባህር በር ሕጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለማስመለስ የጀመረችዉን እንቅስቃሴ ተከትሎ በካይሮና አስመራ ትልቅ ድንጋጤ ተፈጥሯል።

የብሪክስ አባል ሃገራትን ጨምሮ የሌሎች ሃገራት መሪዎችና አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ድጋፍና ተጽእኖ መጠር መጀመራቸዉም የካይሮና አስመራ ቤተ መንግስቶችን ተጨማሪ ሃዘን ዉስጥ ከቷል።

ሻዕቢያና ህገወጡ የህወሃት ቡድንን በመርዳት የከሰረችዉ ግብጽ በቅርቡ የኢትዮጵያን የባህር በር ጉዞ ለማደናቀፍ ጽምዶ የሚባል አላማ ቢስ ጥምረት ብትፈጥርም ጥምረቱ እርስ በርሱ መግባባት አለመቻሉም አስመራንና ካይሮን እረፍት እየነሳ መሆኑንም መረጃዎች ያመላክታሉ።

በርካታ አለም አቀፍ የፖለቲካ ተንታኞች ጽምዶ የተባለዉ ስብስብ መንግስትን መገዳደር የማይችል ተራ ጥምረት መሆኑን እየተናገሩ መሆናቸዉም ጽንፈኞችን ተስፋ አስቆርጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጥምረቱን በበላይነት የሚመራዉ ህገወጡ የህወሃት ቡድን የትግራይ ክልልን ሠላም በማደፍረስ በአማራና በአፋር ክልሎች እያደረገ ያለዉ የጦርነት እንቅስቃሴ በአለም አቀፉ ህብረተሰብ እየተወገዘ ይገኛል።

ዉግዘቱን ተከትሎም በካይሮ ቤተ መንግስት ትልቅ ተጨማሪ ስጋት መፈጠሩን ነዉ መረጃዎች የሚያመላክቱት።

በሃገሩ ሉዓላዊነትና ህልዉና የማይደራደረዉ ጀግናዉ የሃገር መከላከያ ሠራዊት ከለዉጡ በኋላ የገነባዉ ትልቅ ወታደራዊ አቅምም የምስራቅ አፍሪካን ሠላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚችል አስተማማኝ ሃይል መሆኑም በቀጣናዉ ለሚንቀሳቀሱ የጸረ ሠላም ሃይሎች ትልቅ ስጋት ሆኗል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review