AMN – መስከረም 23/2019 ዓ.ም
የሆራ ፍንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የዕርቅ እና የባህላዊ እሴቶች መገለጫ መሆኑን የኦሮሞ አባ ገዳዎች ማህበር ሊቀመንበር እና የመጫ አባ ገዳ ወርቅና ተሬሳ ገለጸዋል።
የኦሮሞ አባ ገዳዎች ማህበር ሊቀመንበር አባ ገዳ ወርቅና ተሬሳ ከኤ አም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በዓሉ ከምስጋና ባሻገር ሰላም፣ ዕርቅ እና አብሮነት የሚታወጅበት ታላቅ የባህል መድረክ መሆኑን አንስተዋል።
ኢሬቻ ማለት ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ብቻ ሳይሆን፣ ማህበረሰቡ ሰላም የሚያውጅበት እና ዕርቅ የሚወርድበት ነው። ሰላም ከማንኛውም ነገር ይበልጣል ያሉት አባ ገዳ ወርቅና ተሬሳ፤ ከራስ ጀምሮ እስከ ቤተሰብ በሁሉም ቦታ የሰላምና የወንድማማችነት አምባሳደር መሆን ይገባል ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች ውስጥ የገዳ ሥርዓት እንዲገባ መደረጉ እንዲሁም ህዝቡ ወደ ቀደመው እሴቱ እንዲመለስ የሚደረጉ ሥልጠናዎችና የንቅናቄ ሥራዎች ትውልዱን ባህሉን፣ እሴቱን እና ታሪኩን በሚገባ እንዲያውቅ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ