AMN- መስከረም 27/2019 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ 1ኛ ዓመት የስራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተወካይ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ግልጽና ውጤታማ የሆነ የአስፈፃሚ አካላትን አደረጃጀት በመፍጠር የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና የተጠሪ ተቋማት የውልና የተናጠል ተግባር በግልጽ በማስቀመጥ ረገድ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግስት ተወካዮች የሆኑት ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና ሃና አርአያሥላሴ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት እና ዓላማ በተመለከተ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል። በመንግሥት አስፈጻሚ ተቋማት መስሪያ ቤቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የታዩትን ውስንነቶች ለመቅረፍ ረቂቅ አዋጁ እንደሚያግዝ እና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩና የህዝቡ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻልና የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳለጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ጥናት የተደረገበት እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ በቂ ግብአት ማግኘት መቻሉን አመልክተዋል። ረቂቅ አዋጁ የተቋማትን አደረጃጀት በግልጽ ማስቀመጥ አመራሮች የመንግስትና የህዝብ ሃብትን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል።

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ አንዳንድ የተጠሪ ተቋማት ለውጥ የስራ ባህሪያቸውን እና ያላቸውን ፋይዳ ያገናዘበ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ ቀልጣፋና ውጤታማ አደረጃጀት በመፍጠር የተቋማትን የማስፈጸም አቅምን ለማሳደግ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው፤ የፌዴራል መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት ፣ ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1440/2019 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል።