AMN- ጥቅምት 11/2019 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና ደኅንነት በጽናት ከመጠበቅ ባሻገር፣ የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ህይወት የሚያቀሉ በርካታ የልማት ስራዎችን በማከናወን ሕዝባዊነቱን እያረጋገጠ ይገኛል።
በከፍተኛ የስነ-ምግባርና ብቃት የታነጸው ሠራዊቱ፣ የከተሞች የልማት እንቅስቃሴዎች እና የገጠር የግብርናና የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ድረስ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሕዝብ እውነተኛ አለኝታነቱን አስመሰክሯል።
መከላከያ ሠራዊቱ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብሮች ላይ ከሕዝቡ ጎን በመሰለፍ ተሳትፎ ያደርጋል። የሀገርን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ሂደትም ሠራዊቱ ሰብል በሚሰበሰብበት ወቅት የአርሶ አደሩን ድካም ለመቀነስ በስፋት ይንቀሳቀሳል።
በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ በሚሹ አካባቢዎች ሰብል በመሰብሰብና የእርሻ ስራዎችን በማገዝ ኅብረተሰቡ ፈጥኖ ወደ ምርታማነት እንዲመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ለማንኛውም ሀገራዊ ጥሪ ራሱን ዝግጁ ያደረገው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ መንገዶችና ድልድዮች መልሶ በመገንባትና በመጠገን ለአገልግሎት በማብቃት ሕዝባዊ አጋርነቱን አሳይቷል።
ይህ የሠራዊቱ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የሕዝቡን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ከማቃላል ባለፈ፣ የሕዝብና የሠራዊቱን ትስስር በይበልጥ አጠናክሮታል፡፡ ሕዝቡም ለሀገር ሉዓላዊነት ህይወቱን አሳልፎ ለሰጠው የመከላከያ ሠራዊት ያለውን አክብሮትና ድጋፍ በተለያዩ ጊዜያት አሳይቷል።
በዛሬው ዕለትም በአማራ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ሀገር አፍራሽ የሆኑ የባንዳና የባዳዎችን የጥፋት እኩይ ሴራ የሚያወግዝ እና ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለውን አጋርነትና ድጋፍ የሚያረጋግጥ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በትዝታ መንግስቱ