AMN- ጥቅምት 22/2019 ዓ.ም
እውነተኛ ልማት የሚለካው የሰዎችን ሕይወት በምን ያህል ደረጃ እንደቀየረ በሚያሳየው ውጤት እንደሆነና ይህም በከተማዋ በተጨባጭ እየታየ መሆኑ ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ ለልማት ፕሮጀክቶች መሬት ስታውል የዜጎቿን መብት፣ ጥቅምና የኑሮ ሁኔታ በማክበር ልማትን ከሰው ሕይወት ጋር አስተሳስራ እየሠራች ይገኛል፤ የቦሌ ሹቡ ኤጀርሳ ነዋሪዎች መንደርም የዚህ አካሄድ ጉልህ ማሳያ ነው።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ለሀገራዊ የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ሽግግር ትልቅ አቅም የሚፈጥር ፕሮጀክት ቢሆንም፣ የልማቱ ተነሺዎች የነበራቸው የኑሮ ዘይቤና ማኅበራዊ ትስስር እንዳይጎዳ ልዩ ትኩረት ተደርጎለታል።
በዚህም መሠረት በ17 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የተገነባው የሹቡ ኤጀርሳ መንደር ለነዋሪዎች ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶችን ከማቅረብ ባለፈ፣ የወተት ላም ማርቢያ ሼዶችን፣ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያዎችን፣ የንግድ ሱቆችን እና የምርት መሸጫ መጋዘኖችን፣ እንዲሁም ወፍጮዎችን እና ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶችን በአንድ ላይ አካቷል።

ከዚህም ሌላ መንደሩ የሕፃናት ማቆያና መጫወቻ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ እና የማኅበረሰብ መሰብሰቢያ አዳራሽ በማካተት የቤተሰብን ሕይወት በሁሉም ዘርፍ ለማሻሻል የሚያስችሉ ሁለገብ መሠረተ ልማቶችን አሟልቶ መያዙን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።