AMN- ጥቅምት 24/2019 ዓ.ም
አዲስ አበባ ዛሬ በፈጣን የለውጥ ግስጋሴ ውስጥ ትገኛለች። የከተማዋ መልክ በየዕለቱ እየታደሰ፣ እጅግ የተዋቡ ኮሪደሮችና የወንዝ ዳርቻዎች ተሰርተው የከተማወን ዘመናዊነት እያወጁ ይገኛሉ።
ልማት መለኪያው ውብ አስፋልትና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ብቻ ሳይሆኑ የወገኖችን አቅም ማነስ የሚደጉም ፣ የህፃናትን ፊት በሳቅ የሚሞላ እና የዜጎችን ሰብአዊ ክብር የሚጠብቅ መሆኑን አዲስ አበባ በተግባር አሳይታለች፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸው የልማት ስራዎች በቀጥታ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የማሕበረሰብ ክፍሎች እና አቅመ ደካሞችን ኑሮ የሚያሻሽሉ ማህበራዊ ልማቶችን አጠናክሮ ሲያከናውን መቆየቱ ልማቱን የተሟላና ፍትሃዊ ያደርገዋል።
የትምህርት ቤት ምገባ ፣ የጤና ተቋማት ተደራሽነትን ማስፋት እና የአቅመ ደካሞች የቤት ማደስ ሥራዎች ማሕበራዊ ፍትህን የሚረጋግጡ የከተማ አስተዳደሩ ሰው ተኮር ልማቶች ማረጋገጫ ናቸው።
ሰው ተኮር ልማት ከሚገለጽባቸው ዋና ዋና ማሳያዎች አንዱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተረስተው የነበሩ አረጋውያንን፣ አቅመ ደካሞችን እና አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎች ናቸው።
በክረምት ወራት በጉልበትና በሃብት ማነስ ምክንያት አፍርሶ መገንባት ቀርቶ ጣራ መጠገን አቅቷቸው ዝናብ ሲመጣ በስጋት ይኖሩ የነበሩ አዛውንቶች ቤቶች በዘመናዊ መልኩ ታድሰዋል።
በበጎነት መንደር በተገነቡ ቤቶች አስታዋሽ አጥተው የነበሩ የሀገር ባለውለታዎች ፣ አረጋውያን ፣ አቅመ ደካሞች ቤት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
ጎስቋላ አካባቢዎች ሲታደሱ በዛ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ማሕበረሰቦችንም የልማቱ ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ በመከናወኑ የአዲስ አበባ የመዘመን ግስጋሴ ሁሉንም ማሕበረሰብ ያቀፈ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በመዲናዋ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚተገበረው የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ-ግብር የሺዎችን ሕይወት የቀየረ ትልቅ ስኬት ሆኗል።
ከዚህ ቀደም በርካታ ህጻናት ባዶ ሆዳቸው ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ ስለሚገደዱ ብዙዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ መቆየት አቅቷቸው ከትምህርት ይሰናከሉ ነበር።
ዛሬ ላይ ተማሪዎች በቂና ተመጣጣኝ ምግብ እንዲያገኙ በመደረጉ የተማሪዎችን ትምህርት የመከታተል መጠን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል። የፈተና ውጤቶችም መሻሻላቸውን መምህራን ይመሰክራሉ።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ምን እመግባለሁ የሚለው ጭንቀትም እንዲቀል አድርጓል።
አዲስ አበባ በጤናው ዘርፍ የዘረጋቻቸው መሰረተ ልማቶች ዝቅተኛ አቅም ያላቸውን ዜጎችም ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
የጤና ጣቢያዎች ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሟሉላቸው መደረጉ፣ ዜጎች በአቅራቢያቸው በተመጣጣኝ ዋጋ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ አስችሏል።
በመንግስት ጤና ተቋማት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችና መድኃኒቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ወይም በነፃ እንዲገኙ መደረጉ ለአቅመ ደካሞች ትልቅ ድጋፍ ሆኗል። እናቶች ያለስጋት እንዲወልዱና ህጻናት ክትባቶችን በሰዓቱ እንዲያገኙ መደረጉ የከተማዋን የማህበራዊ ደህንነት አጠናክሮታል።
ልማት መለኪያው ውብ አስፋልትና ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎች ብቻ ሳይሆኑ የወገኖችን አቅም ማነስ የሚደጉም ፣ የህፃናትን ፊት በሳቅ የሚሞላ እና የዜጎችን ሰብአዊ ክብር የሚጠብቅ መሆኑን አዲስ አበባ በተግባር አሳይታለች፡፡
በታደሰ ሽፈራው