የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት-አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ

You are currently viewing የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግ ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት-አፈ ጉባኤ አሕመድ ሽዴ

AMN- ጥቅምት 25/2019 ዓ.ም

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ለማድረግና የሀገሪቱን የተቋማዊ አቅም ለማጠናከር ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበት ገለጹ።

አፈ ጉባኤው ይህን ያሉት ለ7ኛው ምክር ቤት አባላትና ለምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት አመራሮች በተዘጋጀ የሥልጠና መድረክ ላይ ነው።

በንግግራቸውም ባለፉት ስምንት ዓመታት የአገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማሻሻያዎች መከናወናቸውንና በዚህም በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የልማት ደረጃ ለማሻገር የሚከናወኑ ተግባራት ዜጋን ማዕከል ያደረጉና በየዘርፉ ያሉ ጥረቶችን በተቀናጀ መልኩ ወደ ተጨባጭ ውጤት የሚቀይሩ መሆን አለባቸው።

በዚህ ሂደትም የሀገሪቱን ሀብት፣ የሕዝቧን እውቀትና ተነሳሽነት፣ እንዲሁም የተቋማትን አቅም ማሰባሰብና ማቀናጀት ወሳኝ ነው።

የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት በዕቅድና በአፈጻጸም ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ላይ በሚያመጣው ተጨባጭ ለውጥም መመዘን እንዳለበት አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

በዚህ አንጻር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕግ አውጪነት፣ በሕዝብ ውክልናና በሥራ አስፈጻሚው ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር አማካይነት፣ ሀገራዊ ራዕይ ወደ ተቀናጀ አፈጻጸምና ዘላቂ የዜጎች ጥቅም እንዲለወጥ የራሱን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል።

የነገዋ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፣ ምርታማና መሪ አገር እንድትሆን ለማድረግ ምክር ቤቱ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዳለበትም አጽንዖት ሰጥተዋል።

ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከምንጊዜውም በበለጠ በብቃት በመወጣት፣ የተቋማትን አቅም ለማጠናከርና የሕዝብን እምነት ለማሳደግ መሥራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ይህም የተሰጠንን ኃላፊነት መወጣት ብቻ ሳይሆን፣ ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑን በመረዳት የኢትዮጵያን የታላቅነት ራዕይ ለማሳካት በልዩ ትኩረት መሥራት ከምክር ቤቱ የሚጠበቅ ቀጣይ የቤት ሥራ መሆኑን ለአባላቱ አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review