78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ስብስባ ዛሬ ይጀመራል

You are currently viewing 78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ስብስባ ዛሬ ይጀመራል
  • Post category:ዓለም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርከ( ኤ ኤም ኤን )መስከረም 7/2016 ዓ.ም

በ78ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ስብስባ ዛሬ ይጀመራል።

በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ የተለያዩ አገራት መሪዎች የተመድ ዋና መቀመጫ ወደ ሆነችው ኒው ዮርክ በመግባት ላይ ይገኛሉ።

ጠቅላላ ጉባኤው በአምባሳደሮችና በቋሚ መልዕክተኞች ደረጃ ነሐሴ 30/2015 መጀመሩ ይታወቃል።

“መተማመንን ዳግም መገንባት እና ዓለም አቀፍ አጋርነትን እንደገና ማደስ፤ የአጀንዳ 2023 እና የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ በማፈጠን ለሁሉም ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነትን መፍጠር” የጉባኤው መሪ ቃል ነው።

በጉባኤው አገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርን መሰረት በማድረግ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ።

የ78ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ፕሬዝዳንትና የትሪንዳድና ቶቤጎ ዲፕሎማት ዴኒስ ፍራንሲስ ጉባኤው ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥና ዘላቂነት ላይ ያተኮሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬና ነገ የአገራት መሪዎች የሚሳተፉበት የዘላቂ ልማት ግቦች ጉባኤ እንደሚካሄድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤውን አስመልክቶ ካወጣው መርሐ-ግብር ለማወቅ ተችሏል።

ጉባኤው የልማት ግቦቹን የእስከ አሁን አፈጻጸምና ቀጣይ ትግበራ ላይ እንደሚመክር ተገልጿል።

ወረርሽኝን አስቀድሞ መከላከል፣ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች መከላከልና ምላሽ የጤና አገልግሎት ሽፋን ውይይት ከሚደረግባቸው አጀንዳዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በቅርቡ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ በ78ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጓን መግለጻቸው ይታወቃል።

ጉባኤው በ174 አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል ያሉት አምባሳደር መለስ፤ ወደ ስፍራው የሚያቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ በ55 አጀንዳዎች ላይ ንግግር በማድረግ የኢትዮጵያን አቋም ይፋ ያደርጋልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ መድረኩን በመጠቀም አጋሮቿን በማብዛት ብሔራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡና አህጉራዊ አጀንዳዎች እንዲሳኩ ለማድረግ በቂ ዝግጅት ማድረጓን ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር እንደምትሰራ ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የ78ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ስብስባ እስከ መስከረም 15/2016 ይቆያል።

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

YouTube ➲ http://bit.ly/3itThRr

Telegram ➲ http://bit.ly/3W4puw9

Facebook ➲ https://bit.ly/3CJVgI8

Twitter ➲ http://bit.ly/3IKQ3TZ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review