AMN – ጥቅምት 11/2017 ዓ.ም
8ኛው ዓመታዊ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የትብብር ምክክር መድረክ በሕብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በምክክር መድረኩ፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝን ጨምሮ የተቋማቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመርሐ-ግብሩም፤ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትብብር ማዕቀፎች አፈጻጸም እንደሚገመገም ተመላክቷል።
ሁለቱ ተቋማት ሰላም እና ደህንነትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ያላቸው ትብብር ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ምክክሩን አስመልክቶ ከሰዓት በኋላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ለማወቅ መቻሉን የህብረቱ መረጃ ጠቁሟል።
አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ የስራ ቆይታ ለማድረግ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወቃል።
ዋና ፀሐፊው እድሳት የተደረገለትን የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ሕንጻን ይመርቃሉ ተብሎም ይጠበቃል።