84ኛው የሳምቤ የአርበኞች ድል መታሰቢያ በኢሉአባቦር ዞን ተከበረ

You are currently viewing 84ኛው የሳምቤ የአርበኞች ድል መታሰቢያ በኢሉአባቦር ዞን ተከበረ

AMN ሚያዝያ 27/2017

የሳምቤ አርበኞች ፋሺስት ጣሊያንን ድል ያደረጉበት 84ኛው የመታሰቢያ ቀን በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ ኢኖስ ሳምቤ ቀበሌ ተከብሯል፡፡

የኢሉባቦር ዞን ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ወንድሙ ደበላ 84ኛውን የሳምቤ የአርበኞች ድል መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የሳምቤ ጀግኖች የጣሊያንን ጦር ድል ባደረጉበት በታሪካዊዉ ቀበር ወንዝ ላይ የተገነባዉ ተገጣጣሚ ድልድይ መመረቁን ተናግረዋል፡፡

የአሌ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጌታቸዉ በበኩላቸዉ የሳምቤ ድል መላዉ ኢትዮጵያዊያን ለሃገራቸዉ ነጻነትን ሉአላዊነት የጋራ ተጋድሎ ስለማድረጋቸዉ ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡

በበአሉ አከባበር ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ለሃገራቸዉ አንድነትና ሉአላዊነት በጋራ ተዋግተዋል፤ በጋራም ድል አድርገዋል የሳምቤ ድልም ለዚህ ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡

አዲሱ ትዉልድ ባለዉ እዉቀት፤ ሙያና አቅም ድህነትን በማሸነፍ ጀግኖችን ሊዘክር እንደሚገባም አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ አሳስበዋል፡፡

ሳምቤ በኦሮሚያ ክልል በኢሉአባቦር ዞን አሌ ወረዳ በጥንታዊቷ ጎሬ ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ስፍራ ነው።

ፋሺስት የጣሊያን ጦር በአድዋ ጦርነት የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ወደ በ1933 ዓ.ም ወደ ጥንታዊቷ ጎሬ ከተማ አቅራቢያ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በአካባቢዉ ጀግኖች የተባባረ ክንድ ዳግም ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡

ምሁራን እንደሚናገሩት ከሆነ ሳምቤ ለፋሺስት ጣሊያን የመጨረሻው አውደ ውጊያ ነዉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review