
AMN-ኅዳር 18/2017 ዓ.ም
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት Ethiopian Remote Sensing Satellite -2 (ETRSS-2) የሚል ስያሜ የተሰጣትን ሶስተኛዋን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በጋራ አልምቶ ለማምጠቅ በያዘው ዕቅድ መሰረት አለም አቀፍ ግልፅ ጨረታን በመከተል የተካሄደው የግዢ ስርዓት ተጠናቆ የውል ስምምነት ሰነድ አሸናፊ ከሆነው ከቻይናው Shangai Engineenring Centre of Microsatellite ጋር ተፈራርሟል።
ይህን የውል ስምምነት ሰነድን የስፔስ ሳይንስን እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ እና የShangai Engineenring Centre of Microsatellite ም/ዋና ዳይሬክተር Xiaocheng Zhu said ፈርመውታል።

በመፈራረሚያው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ፎዚያ አሚን (ዶ/ር) ለስምምነቱ ተግባራዊነቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ እንዳሉት ሁለተኛው የኢትዮጵያ የመሬት ምልከታ ሳተላይት (ETRSS-2) በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚመረት እና ወደ ስራ ከገባ በኋላ ለ5 ዓመታት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም ወደ ህዋ ካመጠቃቸው ሁለቱ ሳተላይቶች ከፍተኛ ልምድ በማካበቱ በቀጣይም ETRSS-2 አልምቶ ወደ ትግበራ ሲገባ የሰብል፣ የደን እና የውሃ ክትትልና ቁጥጥር ማዕከላት እንዲሁም የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የተፈጥሮ አደጋ ስጋት መከላከል ማዕከላት ውሳኔ ሰጭነት እና ለፖሊሲ ቀረጻ ድጋፍ ለመስጠት ወቅታዊ መረጃ ይሰጣል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአለም ፈር ቀዳጅ ስልጣኔ ካላቸው ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች በመሆኑም የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂ የቅንጦት ሳይሆን የኢትዮጵያን መፃይ የእድገት መሠረቷ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።