ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ( ዶ/ር)

ምክክር የሰው ልጅ አብሮ የመኖር ምሰሶ ነው፡፡ በሰው ልጅ የህልውና ካሴት ውስጥ ምክክር እንደ ወርቃማ ክር ክፉውን አስረስቶ ደግ ደጉን በለሆሳስ እያሰማ ነፍስያን በፍቅር ያስደስታታል፤ ስጋንም በአንድነት ወዝ ያደምቃታል፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ ደግሞ እንደ ሸማኔ መወርወሪያ አንዱን ከአንዱ እያስተሳሰረ ይኖራል። ግጭትና ብጥብጥ ባለበት ዓለም፤ ምክክር የሰላም፣ የአብሮነት እና የተስፋ መስታወት ሆኖ የቆመ፣ የእርቅና የሰላም መንገዶችን የሚያደምቅ ብርሃን እንደሆነ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን ይናገራሉ፡፡
ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ደግሞ “ምክክር እውነትን የምንፈልግበት መንገድ ነው” ይላሉ፡፡ ምክክር የተደበቀን አሊያም ያልታወቀን እውነት የምንፈልግበት መሳሪያ ነው፡፡
ይህ ማለት ስንነጋገር እና ስንመካከር እንተዋወቃለን፡፡ ስንነጋገር፣ መስመር መስመር እየያዝን ስንሄድ በተለይም ህሊናችን ውስጥ የተደበቀው ያ! እውነት ከውስጥ ይወጣል፡፡ ለዚህም ነው ምክክር የዕውነት ፍለጋ መንገድ ነው ተብሎ የሚታመነው ብለዋል ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር)፡፡
በሀገራችን ልዩ ልዩ ባህሎች አውጫጭኝ፣አፈርሳታና መሰል የእውነት ማውጫ መንገዶች አሉ፡፡ እነዚህ እሴቶች በመመካከር ከውስጥ የተቀበሩ ችግሮቻችንን ማውጫ መንገዶች ናቸው። እውነት ስንል ደግሞ አንዳችን በሌላችን ቦታ ሆነን ችግሮቻችንን ተመካክረን የምናወጣው እውነት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ችግሮቻችንን ስንነጋገር፣ ስንረዳዳ እውነት ይወጣል፡፡ እውነት ሲወጣ ደግሞ የጋራ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን፡፡ በተግባርም በደቡብ አፍሪካ፣ በኬኒያ፣ በሩዋንዳ እና መሰል ሀገራት ይህንን እውነት አይተናል፡፡ ይቅር ተባብሎ ወደ እርቅ መምጫ ስለሆነ ምክክር የእውነትን መፈለጊያ መንገድ ነው የሚባለው ለዚህ እንደሆነም አክለዋል፡፡
የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ጥረት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ያለው አስተዋፅኦ ከፍ ያለ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነር ዮናስ( ዶ/ር) እንደ ሀገር ሁሉም ባለድርሻ እንደሆነ ጠቅሰው በዋናነት ግን መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የሀይማኖት መሪዎች እና ምሁራን ካላቸው ኃላፊነት እና ተፅእኖ ፈጣሪነት አንፃር ትልቁን ሚና ይጫወታሉ ብለዋል፡፡
እንደ ሀገርም የባለድርሻ አካላት ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለነው፡፡ የሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ ይህንኑ እንደሚያሳይ የጠቀሱት ኮሚሽነር ዮናስ(ዶ/ር) ለአብነትም ፖላንድ ላይ ባለድርሻ አካላት እራሳቸው የምክክር ኮሚሽን አቋቁመው መንግስት እስከ ማቋቋም የደረሱበትን ታሪክ እንዲሁም በቱንዚያም ሲቪክ ማህበራት ያቋቋሙትን ሀገራዊ ምክክር በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያም መንግስትና ህዝብ ሀገራዊ ምክክርን እንዳቋቋሙም ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም ሀገር በምክክር ችግሯን ትፈታ ዘንድ ባለድርሻ አካላት እስካሁን ካደረጉት የበለጠ ህዝቡን ስለምክክር አስፈላጊነት፣ ሂደት፣ መድሃኒትነት በተለይም ለዘመናት የተከማቹ ችግሮቻችን መፍቻ መንገድ ምክክር በመሆኑ ይህንን ህዝቡን በማስተማር እና ወደ እውነት ፍለጋ ሂደት ሁሉም እንዲሰማራ እና በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ በማድረግ ከፍተኛ ሚናቸውን መጫወት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ኃይማኖተኝነት፣ ፈጣሪን መፍራት፣ መከባበር፣ መተዛዘን፣ መደጋገፍ ባህላዊ እሴት አሉት፡፡ እነዚህ እሴቶች ኢትዮጵያን ለሺህ ዘመናት እንደ ክር በማስተሳሰር በአንድነት እንድትቀጥል አድርገዋል፡፡ በሀገራዊ ምክክሩ ባህላዊ እሴቶችን ወደ ወረት ወይም ካፒታል በመቀየር ሀገርን ለማሻገር እየተሰራ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡
በመከባበር፣ ዝቅ በማለት፣ በመደማመጥ፣ ችግሮችን መፍታት፣ ህይወትን ማደስ ይቻላል፡፡ የፈለገ ግጭት ቢኖር በመደማመጥ መፍታት ይቻላል፡፡ የሩዋንዳንም ማየታቸውን የሚናገሩት ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር)፤ ሀገር በቀል የመነጋገሪያ መድረኮች ምን ያህል አዋጪ መሆናቸውን እንዳረጋገጡበት ይጠቅሳሉ።
እንደ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መረጃ ከሆነ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር እሴቶች፡-
አካታችነትና አሳታፊነት፣ ገለልተኛነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ብቃትና ሙያተኛነት፣ አጋርነትና ትብብር፣ የህግ የበላይነት፣ ተዓማኒነትና ቅቡልነት እና የባለድርሻ አካላት አስተዋፅኦ ናቸው፡፡
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ሂደትን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያዘጋጀው አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዶ ነበር። በዚህ አውደ ጥናት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባሳደር መሀሙድ ድሪር የባለ ድርሻ አካላት ትብብር እስካሁን በነበረው የምክክር ሂደት ያጋጠሙ ውጣ ውረዶችን ለማለፍ ጉልህ እገዛ ማድረጉን አንስተዋል።
ይህ በጋራ ጉዳይ አብሮ የመስራት ባህል በቀጣይ ለሚከናወኑ የምክክር ሂደቶችም ወሳኝ እንደሆነ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው በአመለካከትና በሀሳብ የተራራቁ አካላትን አሰባስቦ በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረግ ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
ምክክር እውነትን የምንፈልግበት መንገድ ነው ያሉት ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) አንዱ የአንዱን ችግር የሚረዳው ምክክር ሲያደርግ ብቻ ነው ሲሉም አክለዋል። ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ የምክክር ሂደትን ባህል ለማድረግ እየተካሄደ ባለው ተግባር ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነውም ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት እያካሄደ ያለው የምክክር ሂደት እስከ አሁን ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ሀገራዊ መግባባትን ለማጠናከር ቁልፍ የሆነውን የምክክር ሂደት ባህል ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሀገራዊ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና እድገትን ለማረጋገጥ በኮሚሽኑ የተጀመረው ጥረት ከግብ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደት የብዙ ከዋኞችን ተሳትፎ የሚፈልግ የዲሞክራሲ እና የሰላም ግንባታ ሂደት ነው፡፡ ሂደቱ በርካታ ባለድርሻ አካላትን የሚያሳትፍ ሆኖ በተለያየ የዕድሜ ወሰን ውስጥ የሚገኙ፣ በተለያየ የሕይወት ተሞክሮ ውስጥ የሚያልፉ እና በማህበረሰባቸው ውስጥ የተለያየ ሚና የሚጫወቱ ዜጎችን ያሳትፋል፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያም እየተካሄደ የሚገኘው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የትውልዶችን ተሳትፎ እና መስተጋብር በማበረታታት እና በጋራ ችግሮቻቸው ላይ መነጋገር እንዲጀምሩ በማድረግ አበረታች ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡
ሀገራዊ ምክክሮች አካታች በሆነ መንገድ መካሄዳቸው የሀገሪቱን ችግሮች በመፍታት ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ እየዳበረ የሚሄድ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት የሆነች፣ ዘላቂ እና ፍትሃዊ እድገት የሚመዘገብባት ኢትዮጵያን የማየት ተስፋን እውን ለማድረግ ሀገራዊ ውይይት አስፈላጊ መሆኑ በአዋጁ ተብራርቷል።
ሀገራዊ ምክክር ግቡ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር እና ለማጎልበት እንዲሁም ሀገራዊ መግባባት ሊኖርባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አካታች የምክክር እና የውይይት ሂደት በመፍጠር፤ ሰፊ መሠረት ያለው ስምምነት፣ መግባባት እና የጋራ አቋም እንዲኖር ማድረግ ነው።
በተቻለ መጠን መሠረታዊ የሚባሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በተለያየ ጎራ የተሰለፉ የፖለቲካ ልሂቃንም ሆነ ምልዐተ ሕዝቡ ተቀራራቢ እና ለሀገራዊ አንድነት ገንቢ የሆነ አቋም እንዲይዙ ማድረግ የአካታች ሀገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ግብ መሆኑ በአዋጁ ላይ ተመላክቷል።
በመለሰ ተሰጋ