AMN-የካቲት 21/2017 ዓ.ም
በአዲስ ከተማ ክፍለ-ከተማ ወረዳ 7 በተለምዶ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመኖሪያ እና ንግድ ቤቶች ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሃመድ ለኤ ኤም ኤን እንደገለፁት፣ አደጋው ዛሬ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከሌሊቱ 10:35 ሰዓት ነው የተከሰተው።
የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር በተደረገው ሰፊ ርብርብ አሁን ላይ አደጋውን መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።
አደጋ የደረሰበት ቦታና አካባቢ በከተማ ደረጃ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ ከተለዩ የመኖሪያና የንግድ አካባቢዎች አንዱ መሆን የገለፁት ኮሚሽነሩ ቤቶቹ የተገነቡበት ግብአት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዉ እንዲሁም የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎችን አለማስገባቱ ተደማምሮ የእሳት አደጋዉ እንዲሰፋ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
በእሳት አደጋዉ በሰዉና በንብረት ላይ የደረሰዉን ጉዳት እንዲሁም የአደጋዉ መንስዔ ተጣርቶ እንደሚገለጽ ተመላክቷል።
የእሳት አደጋዎችን ለመከላከል ለጥንቃቄ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።