የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ከሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም ራሱን በየጊዜው እየገመገመ በሁለንተናዊ መስኩ እያበቃ የመጣ ሀገሩን የሚወድና የተሰለፈበትን ዓላማ ጠንቅቆ የተረዳ ፕሮፌሽናል ሠራዊት መገንባቱን ገልፀዋል።
በሀገሪቱ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በተቋሙ የተሰራው ሪፎርም በርካታ ውጤቶች ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ማስቻሉንም አንስተዋል።
ሀገራችን በታሪኳ በዚህ ደረጃ ብዛትና ጥራት ያለው የፕሮፌሽናል ሰራዊት ገንብታ አታውቅም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ፣ ሀገሩንና ሙያውን የሚወድ የሚሰጠውን ግዳጅ በአነስተኛ ኪሳራ የመፈፀም ብቃት ያለው ሀይል ተገንብቷል ብለዋል።
ሠራዊቱ ሀገርን ከብተና ከማዳን ባለፈ የሀገሪቱን ሰላም ፣ ብልፅግናና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት ያስመዘገባቸው ድሎች በታሪክ ሲዘከር የሚኖር መሆኑንም ገልፀዋል።
በተገኙ ድሎች ባለመኩራራት የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ድሎች አጠናክሮ ለማስቀጠልና የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ማረጋገጣቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።