ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ለሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ስኬታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

AMN – ታኅሣሥ 5/2017 ዓ.ም

ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ውጤታማነት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ የፍትህ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ስላሴ ጥሪ አቀረቡ።

ሚኒስትሯ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ አምባሳደሮች እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ ምዕራፍን አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል።

ፖሊሲውን አስመልክቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ ከ80 በላይ ውይይቶች ላይ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፖሊሲውን ማጽደቁን ተከትሎ የፍትሕ ሚኒስቴር የፖሊሲ ማስተግበሪያ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን አመልክተዋል።

የሽግግር ፍትህ ማስተግበሪያ ስልቶችን የሚተገብሩ ተቋማትን ማቋቋም የሚያስችሉ የህግ ረቂቆች መዘጋጀታቸውንም ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች በኋላ ረቂቆቹ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልከው እንደሚጸድቁ ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት።

የሚቋቋሙት ተቋማት በህግ የሚጣልባቸውን ኃላፊነት መወጣት በሚያስችላቸው ደረጃ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው በሚቋቋሙበት ሁኔታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ፖሊሲው የወንጀል ተጠያቂነት፣ እውነትን ማውጣት፣ ቅድመ-ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምህረት፣ ማካካሻ እና ተቋማዊ ማሻሻያ ላይ ያተኮረ እንዲሁም ባለፉት አመታት የተፈጸሙ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እልባት በመስጠት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ውጥን መያዙን አብራርተዋል።

የዓለም አቀፍ ተቋማት እና የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ጨምሮ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እያከናወነቻቸው ያሉ ተግባራትን እንዲደግፉም ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ መጠየቃቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review