AMN-ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፅናት ለኢትዮጵያ እና ከሰላም እና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበራት የተሰባሰቡ አጀንዳዎችን ከማህበራቱ ተወካዮች ተቀብሏል፡፡
መቀመጫቸውን በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በማድረግ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውኑ የቆዩት እነዚህ ማህበራት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ይገባል ብለው ያመኑባቸውን የምክክር አጀንዳዎችን ዛሬ ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡
የማህበራቱ ተወካዮች በኮሚሽኑ ፅ/ቤት በነበራቸው ውይይት በቀጣይም ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመስራት በሀገራችን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የምክክር ሂደት ለመደገፍ ያላቸውን ፈቃደኝነት ገልፀዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕሮፌሰር) የማህበራቱን የእስካሁን እንቅስቃሴ አድንቀው የዲያስፖራው ማህበረሰብም በተለያዩ መንገዶች አጀንዳዎቻቸውን በመስጠት በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡
ፅናት ለኢትዮጵያ እና ሰላም እና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበራት “በምክክር ሀገር ትዳን” በሚል መሪ ሃሳብ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማድረግ እና የማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳዎችን በመስራት ለኮሚሽኑ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ኮሚሽኑ አስታውሷል።