መጋቢት 24 የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ለተመዘገበው ድል ህዝባችን ያደረገልንን የማያወላውል ድጋፍ እናስታውሳለን፤ ለዚህም እናመሰግናለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
የሀገራዊ ለውጡን 7ኛ ዓመት አስመልክቶ ህብረተሰቡ ለለውጡ መንግስት ያለውን አጋርነት በህዝባዊ ሰልፍ በማሳየቱም አቶ ሽመልስ ምስጋና አቅርበዋል።
በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ‘ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና!’ በሚል መሪ ሐሳብ የሐይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ ተካሂዷል።
የሰልፎቹ ተሳታዎች መንግስት ያስመዘገባቸውን ዘርፈ ብዙ ድሎች አድንቀው፤ በቀጣይ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት አረጋግጠዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ህዝቡ ላሳየው አጋርነት ምስጋና አቅርበው፤ የለውጡ አመራር የጀመረውን ስኬታማ ጉዞ እንደሚያስቀጥል አረጋግጠዋል።

ለውጡን ዕውን ለማድረግ ረጅም ጊዜ የፈጀ ትግል መደረጉን አስታውሰው፤ በለውጡ ማግስት በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ዘርፎች ስኬት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ህዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና ሌሎች ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የህዝብ ቁልፍ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ አመራር መስጠታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የመብት፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሁም የተቋም ግንባታ ላይ የላቀ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በፖለቲካው መስክ እንደ ሀገር ስር ሰዶ የነበረውን የመከፋፈልና የሴራ ፖለቲካ ባህል በመቀየር፤ በምክክር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር የሚያስችል አመራር መፈጠሩን ተናግረዋል።
ለውጡ የሀገራችን ህዝቦች ጥያቄ መመለስ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ እውቅና ያተረፉ በርካታ ስኬቶችን መመዝገባቸውን አውስተዋል።