AMN – መጋቢት 9/2017 ዓ.ም
ህዝባዊነታችንን በተግባር በማሳየት አለም አቀፍ ተመራጭ የሰላም ኃይል ሆነን እንቀጥላለን ሲሉ የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ ገለጹ፡፡
ወደ ደቡብ ሱዳን ጁባ የሚሰማሩት የ20ኛ እና 21ኛ ሞተራይዝድ የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ሻለቃ አባላት ዛሬ ተመርቀዋል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጀኔራል ደስታ አብቼ፣ ሠራዊቱ አሁናዊ አለም አቀፍ የጦርነት ባህሪን በመረዳት ዘመኑ የሚጠይቀውን የውጊያ ቴክኖሎጅ መላበሱን አንስተዋል።
በአለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ያለው ተፎካካሪነት እያደገ በመምጣቱ እኛም ሰው ተኮር መርህን በማስቀደም በሁሉም ዘርፍ ተመራጭ የሰላም ሃይል እየገነባን ነው ብለዋል፡፡

ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ፣ ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለፍጥረታት ሁሉ የሚያስፈልግ ጉዳይ በመሆኑ ዘማች የሠራዊት አባላትም፣ ይህንን በመገንዘብ ለወንድም አፍሪካዊያን ህዝብ ተገቢውን ከለላ በማድረግ ኢትዮጵያዊነታችንን በአለም አደባባይ ከፍ ማድረግ ይጠበቅባችኋል ነው ያሉት።
የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማሰልጠኛ ማዕከል አዛዣ ሜጄር ጄኔራል አዳምነህ መንግስቴ በበኩላቸው፣ ተመራቂ የሰላም አስከባሪ የሰራዊት አባላት የሚታወቁበትን ህዝባዊ ባህሪና አንድነት በመጠበቅ ተልዕኮዋቸውን በውጤታማነት መፈፀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የስልጠናውን ሪፖርት ያቀረቡት የሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ፣ ኢትዮጵያ ለአለም ሰላም መረጋገጥ በመስዋዕትነት የታጀበ ዋጋ መክፈሏን ተናግረዋል።
ሰልጣኞች በቆይታቸውም ግዳጃቸውን በብቃት መወጣት የሚያስችላቸውን ትምህርት በንድፈ ሃሳብና በተልዕኮ ተኮር ሥልጠና ቀንና ሌሊት መውሰዳቸውን መናገራቸውን ከመከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።