
AMN- ህዳር 6/2017 ዓ.ም
የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዝግጅት አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ለ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እየተደረገ ያለውን ቅድመ ዝግጅት ለሁለተኛ ጊዜ የአፈፃም ግምገማ አካሂዷል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት መገኛ እና አስተናጋጅ ሀገር እንደመሆኗ መጠን በዘንድሮው ዓመት የሚካሄደውን ይህን ትልቅ የመሪዎች ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት ዘርፈ ብዙ ዝግጅቶች መደረጋቸው ተገምግሟል።
በዚህ ስብሰባ ተቋማት በብሔራዊ ዝግጅት ኮሚቴው አማካኝነት የተሰጡ እቅዶች አፈፃፀማቸው፤ ከተቋማቸው ባህሪ አንፃር መነሻ እና ዝርዝር እቅዶች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል።
ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያን ይበልጥ ለማስተዋወቅ ስለሚያስችል የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና እንዲሁም ደኀንነቱ የተጠበቀ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት የተሟላ ቅንጅት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
ስብሰባውን የመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ መብራቱ እና የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ መላኩ በዳዳ የወጡ እቅዶች በአፈፃፀም እና በትግበራ ምዕራፉ የተዋጣለት እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የካቲት 8 እና 9 ቀን 2017 ዓ.ም.፣ 46ኛው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ደግሞ የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ከመውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ብሔራዊ ኮሚቴው ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተውጣጣ መሆኑም ተጠቁሟል።