
AMN – ታኅሣሥ 15/2017 ዓ.ም
ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈና ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ገለፁ።
ቢሮው ከ47 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው የአይሲቲ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ለክፍለ ከተማ ወረዳ እና ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ነው ተብሏል፡
በአዲስ አበባ ከተማ ለተገልጋዩ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ከተማ አስተዳደሩ በተቋማት ላይ የተለያዩ ሪፎርሞችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
ሪፎርም ካደረጉ ተቋማት መካከልም የአዲስ አበባ ከተማ ስራና ክህሎት ቢሮ አንዱ ነው።
ቢሮው በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
ቢሮው ከ47 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የኮምፒውተር ና ፕሪንተር መሰል የአይሲቲ እቃዎችን ለክፍለ ከተማና ወረዳ እንዲሁም ለቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ድጋፍ አድርጓል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጥራቱ በየነ ቢሮው ከተገበራቸው የለውጥ ስራዎች ውስጥ ለተገልጋዩ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አዲስ የሲስተም ስርዓት ለምቶ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በቢሮው ለምተው ለአገልግሎት የሚበቁ ሲስተሞችን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ና ወረቀት አልባ አገልግሎትን ለመስጠት መታቀዱን ኃላፊው አመላክተዋል።
ይህንኑ ዘመኑን ያልዋጁ አገልግሎቶችን ወደ ቴክኖሎጂ በመቀየር ተቋማቱ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልም ግብዓቶችን የማሟላት ስራ እየተሰራ መሆኑንንም አቶ ጥራቱ ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቶቹን በቴክኖሎጂ አግዞ ለመስጠት የሚያስችሉ ግብዓቶች የተበረከተላቸው ተቋማትም የተደረገላቸው ድጋፍ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
በመሀመድኑር አሊ