የሎጅስቲክስ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ ብቁ እና የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ እንደሚገባ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ለተውጣጡ 100 ወጣት ሴቶች በሎጅስቲክስ ዘርፍ መሰማራት የሚያስችላቸው ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።
በመርሃ-ግብሩ የሚኒስቴሩ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብዱልበር ሸምሱ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አበርክቶ ባለው የሎጅስቲክስ ዘርፍ ቀልጣፋ እና የዘመነ አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት ቁልፍ ጉዳይ ነው።
ስልጠናው ከሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ ሴቶች ማካተቱን ገልጸው ሰልጣኞች በዘርፋ በቂ እውቀት እንዲያካብቱና ምርምሮችን እንዲያርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ስልጠናው በሎጅስቲክስ ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ፣ የአገልግሎት ተወዳዳሪነት ደረጃ ለማሳደግ፣ የስራ ዕድል መፍጠርና በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ መጨመርን ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ስልጠናውን ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ጭነት አስተላላፊዎች ማህበር እና የዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ነው።
ስልጠናው ለስምንት ወራት እንደሚቆይ እና ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋላ ወደ ስራ እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደሚደረግ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።