AMN – ጥር 10/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት ለቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለካፒቴን መሐመድ አህመድ የመታሰቢያ ሀውልት አቆመ።
በመርሀግብሩ ላይ የካፒቴን መሐመድ አህመድ ቤተሰቦቸ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የማኔጅመንት አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ካፒቴን መሀመድ አህመድ በአቪዬሽኑ መስክ ግንባር ቀደም ከሚባሉት አመራሮች አንዱ ሲሆኑ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለንተናዊ ዕድገት ያኖሩት የማይተካ አሻራ በመጪው ትውልድም ሁልግዜ ሲታወሱ እንደሚኖር ተወስቷል፡፡
ካፒቴን መሀመድ አህመድ ከኢትዮጵያ አልፈው የአፍሪካ አየር መንገዶች ህብረትን ለአስር አመታት በመምራት በአፍሪካ አየር መንገዶች መካከል የጠበቀ ግንኙነት እንዲፈጠርና ለአህጉሪቱ የአቪዬሽን ኢንደስትሪ ዕድገት በጋራ የመስራት መንፈስ እንዲጎለብት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
በአለም ዓቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በአመራር ኮሚቴዎች ውስጥ በነበራቸው ሚና የአፍሪካ አየር መንገዶች በአለም መድረክ አድገውና ጎልብተው እንዲወጡ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል።
ካፒቴን መሀመድ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በዋና ስራ አስፈፃሚነት በመሩባቸው ዓመታት አየር መንገዱ ዛሬ ለደረሰበት እድገት እና ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ መገለጹን ከአየር መንገዱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡